ኢትዮጵያ በመደመር መንግሥት ታላቅ የልማት ጉዞ ላይ ትገኛለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በመደመር መንግሥት ታላቅ የልማት ጉዞ ላይ ትገኛለች
ኢትዮጵያ በታሪኳ የታላቅነት፣የሥልጣኔና የሉዓላዊነት ምሳሌ ሆና የኖረች ሀገር ናት።በዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ የራሷን መገበያያ በጥንት ዘመን ፈጥራ፣ ፊደላትን ቀርጻ፣ እንደ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ያሉ ዓለምን ያስደመሙ የኪነ ህንጻ ሥራዎችን የከወነች ኃያል ሀገር ናት።
የስልጣኔ ሀገረ መንግሥት ተብለው ከሚጠቀሱት ጥቂት ሀገራት አንዷ የሆነው ኢትዮጵያ የዓለም ተቋማትን በመመስረት፣ ለግፉዓን ድምፅ በመሆን፣ በዓለም የፖለቲካ አውድ ግዘፍ የነሳውና ብዙ ለውጦችን ያመጣው የዓድዋ ድል ባለቤቷ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ቅስማቸውን በመስበርና በማንበርከክ ድል አድርጋ የአድዋን ታላቅ ድል ለአፍሪካውያንና ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነፃነትና የብሥራት ምልክት አድርጋ አስረክባለች።
ሆኖም ይህ ታላቅ የታሪክ ኩራትና የሉዓላዊነት ወደር የለሽ ክብር ሀገሪቱን ወደ ዘመናዊ የኢኮኖሚ ብልጽግናና ተወዳዳሪነት በበቂ ሁኔታ ሳይቀይራት ለረጅም ዘመናት ቆይቷል።
ታዲያ የዚህ ሁሉ የስልጣኔና የድል ውርስ ባለቤቷ ሀገር እንዴት ወደኋላ ቀረች? በተከታታይ በነበሩ የሥልጣን ሽኩቻዎች፣የውስጥ ግጭቶችና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ምክንያት ሀገራዊ አቅምና የሰው ኃይል ለግንባታ ሳይሆን ለጥፋት ሲውል ቆይቷል።
በተጨማሪም የጠንካራና ዘላቂ ተቋማት አለመገንባታቸው እንዲሁም የፖሊሲ ውሳኔዎች ከተጨባጭ የሕዝብ ፍላጎት ይልቅ በርዕዮተ-ዓለም አክራሪነት ላይ መመሥረታቸው ኢኮኖሚውንም ፖለቲካውንም በእጅጉ ጎድቶታል።ዓለም በኢንዱስትሪ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂና በዘመናዊ ግብርና እየመጠቀች በሄደችበት ወቅት ኢትዮጵያ በባህላዊ የአመራረት ዘይቤና በውጭ እርዳታ ጥገኝነት ውስጥ ታስራ በመቆየቷ ከዓለም አቀፍ ውድድር ወደኋላ ቀርታለች።የሀገር ሀብት፣ የምሁራን እውቀት፣ የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ጥረት ሳይቀናጁና ሳይደጋገፉ በየፊናቸው በመጓዛቸው የታሰበውን ሀገራዊ ስኬት ማምጣት ሳይቻል ቀርቷል።
ይህንን የታሪክና የልማት ክፍተት ለማረቅ የተነሳው የመደመር መንግሥት የትናንትን ጥፋቶች ማረም፣ መልካም ስኬቶችን ማስቀጠልና የነገን ብልጽግና የሚያረጋግጥ አዲስ ሀገራዊ ምዕራፍ መክፈትን ዓላማ አድርጎ ተነሳ።
የመጀመሪያው የትኩረት አቅጣጫ የተበታተኑ ሀገራዊ አቅሞችን ማለትም የሕዝብን፣ የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍ፣ የምሁራንንና የዳያስፖራውን አቅም በማቀናጀት ለጋራ ልማት ማሰለፍ ነው። ሁለተኛው ሀገሪቱን ከእርዳታና ከተወሰኑ ዘርፎች ጥገኝነት በማውጣት ግብርናን፣ አምራች ኢንዱስትሪን፣ ማዕድንን፣ ቱሪዝምንና ዲጂታል ኢኮኖሚን የእድገት መሪ የሚያደርግ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ሪፎርም መተግበር ነው። ሦስተኛው ደግሞ ፕሮጀክቶች በወረቀት ላይ ብቻ ሳይቀሩ በመሬት ላይ ፈጣን፣ ጥራት ያለውና ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጡ የሚያስችል አዲስ የተቋማትና የአፈጻጸም ባህል መገንባት ነው።
የተመዘገቡ ተጨባጭ ድሎች
የመደመር መንግሥት በሁሉም መስክ በትልቁ ማሰብ፣ ጀምሮ መጨረስን ባህል አድርጎታል። በዚህም ኢትዮጵያ እንድታንሰራራ ያስቻሉ ግዙፍ የልማት ምዕራፎችን እያሳካ ይገኛል።
በግብርናው ዘርፍ ኢትዮጵያ የመስኖ ስንዴ ልማትን በማስፋት በዓመት 33 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ በማምረት በአፍሪካ ቀዳሚዋ የስንዴ አምራች ሆናለች። ራሷን ችላም ወደ ውጭ መላክ ጀምራለች። የግብርና ሜካናይዜሽንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማስፋት የሰብል ምርትን ከ335 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ኩንታል ማሳደግ ተችሏል።
በኢኮኖሚና በኢንቨስትመንት ዘርፍ የወጪ ንግድ ገቢን 11 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ማድረስ የተቻለ ሲሆን፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትም 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። በተጨማሪም የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የ15 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት ከውጭ የሚገቡ ስትራቴጂክ ምርቶችን መተካት ተጀምሯል።ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችንም በማምረት ላይ ትገኛለች። በማዕድን ዘርፍም አፈር የለበሱ የከበሩ ማዕድናትን እየገለጠች ወደ ጥቅም በመቀየር ላይ ናት። የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የድንጋይ ከሰል ማምረቻና ማጠቢያዎች የወርቅ ፋብሪካዎችና ግዙፍ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ እየገቡ ናቸው።
የመደመር መንግሥት በመሠረተ ልማትና በሜጋ ፕሮጀክቶች በኩል የትርክትና የአፈጻጸም ለውጥ ፈጥሯል። የማይጠናቀቅ ፕሮጀክት፣ የማይገነባ መሰረተ ልማት የለም በሚል ከለውጡ በፊት የነበሩ የተንከባለሉ ፕሮጀክቶችን በማፋጠን አሳክቷል።ለዚህ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ከነበረበት ውስብስብ የፕሮጀክት አስተዳደር በማላቀቅ በራስ አቅም በዜጎች ደምና ላብ ለውጤት አብቅቷል። ኃይል አመንጭቶ የቀጣናው የብርሃን ማዕከል እንዲሆን አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋ ባደረጓቸው የጉባ ብስራት ሜጋ ፕሮጀክቶችም የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ የጋዝ ማምረቻ፣ የሰላማዊ ኒውክሌር ኃይል ማብለያ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ገብተዋል።
ኢትዮጵያ በመደመር ነገን የተሻለ የማድረግ ሀገራዊ ዕይታ በኮሪደር ልማት ከተማና ገጠሩን ወደ ዘመናዊ የኑሮና የሥራ ማዕከልነት እየቀየረች ትገኛለች።በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ ከአዲስ አበባ በጀመረው የከተማ የኮሪደር ልማት የከተሞችን ውበትና የኑሮ ደረጃ በእጅጉ አሻሽሏል።በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ እየተገነባ ነው።ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ለአፍሪካ ተምሳሌት የሆነች ሀገር መፍጠር ተችሏል።
በቱሪዝምና በሀገር ገጽታ ግንባታ በኩል የገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የተፈጥሮ፣ የታሪክና የባህል ሀብቶችን ወደ ላቀ የኢኮኖሚና የቱሪዝም አቅም ቀይረዋል።የመደመር መንግሥት የቀጣይ ጉዞ ርዕይ ኢትዮጵያን በጠንካራ መሠረት ላይ የቆመች፣ በራሷ አቅም የምትተማመንና በቀጣናው፣በአፍሪካና በዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ማድረግ ነው።
በመጀመሪያ በምግብ ራስን በመቻል፣ የወጪ ንግድ አቅምን በማሳደግና ከውጭ ጫናዎች ነፃ የሆነ ጠንካራ የፋይናንስና የኢንዱስትሪ መሠረት በመገንባት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ በሰላማዊ የፖለቲካ ባህል አማካይነት ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት የተደመረ ሀገራዊ የፖለቲካ ካፒታል የተፈጠረባትና የሕግ የበላይነት የጸናባት ሀገር ማድረግ ነው። ከጎረቤት ሀገራት ጋርም በልማት፣ በኃይል አቅርቦትና በሰጥቶ መቀበል ዲፕሎማሲ ጠንካራ ትስስር የመፍጠር ትልሞችን ማስቀጠል ላይ የመደመር መንግሥት አበክሮ እየሠራ ይገኛል።
የባሕር በርና የንግድ ወጪ አማራጮችን በፍትሐዊነትና በሕጋዊ መንገድ ማረጋገጥ ነው።
በአራተኛ ደረጃ ጥራት ያለው ትምህርት፣የጤና ሽፋንና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽነትን በማስፋት ለነገዋ ዓለም ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል ማፍራት የመደመር መንግሥት ዋና አጀንዳ ነው። የኢትዮጵያ ታላቅ የልማት ጉዞ የትናንት ህልሞችን ወደ ዛሬ ተጨባጭ ድል የመቀየር ሁለንትናዊ ጉዞ ነው።የመደመር መንግሥት ርዕይ ኢትዮጵያን የትናንት ታሪኳን የምትመለከት ብቻ ሳትሆን፣ የነገው ብልጽግናዋ አስተማማኝ የሆነ፣ ዜጎቿ በክብርና በፍትህ የሚኖሩባት ባለታሪክና ባለድል ሀገር አድርጎ ለማስረከብ የትውልድ አደራን በመፈጸም ላይ ይገኛል።