በአዊ ዞን ከ70 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዊ ዞን ከ70 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው
ባህር ዳር፤ ጥቅምት 3 /2019 (ኢዜአ)፦ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከ70 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት በጋ መስኖ እንደሚለማ የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።
የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ስማቸው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው በጋ የውሃ አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም ከ30 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት ሥራ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው።
በዚህም በመጀመሪያና በሁለተኛ ዙር ከ70 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት በነባርና በአዲስ መስኖ ለማልማት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከሚለማው አጠቃላይ መሬትም ከ7ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ አመልክተው በበጋ መስኖ ለማልማት ከታቀደው መሬት ውስጥ 48 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በስንዴ ሰብል የሚለማ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚሁ ወቅት በመስኖ ከሚለማው መሬት ውስጥ 19 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በአዲስ የሚለማ ሲሆን፣ እስካሁን ከ10 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ ለዘር ሥራ ዝግጁ ተደርጓል ብለዋል።
በበጋ መስኖ ልማቱ ስንዴ፣ የቢራ ገብስ፣ ሽንኩርት፣ ጎመንና ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።
ምርታማነቱን ለማሳደግም ለአርሶ አደሩ የዘመናዊ ማዳበሪያ፣ የኮምፖስትና የምርጥ ዘር አቅርቦት እንዲዳረስ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ ጓንጓ ወረዳ አንጓይ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ስሜነህ አያልነህ እንዳሉት፤ በዘንድሮው የበጋ መስኖ በአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ ስንዴ በማልማት ከ40 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት የእርሻ ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ከስንዴ ልማቱ በተጨማሪም ሽንኩርትና ድንች ለማምረት ማቀዳቸውን ነው ያመለከቱት።
በዚሁ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር አልጋነህ አካል በበኩላቸው፤ በአንድ ሄክታር መሬታቸው ላይ ስንዴና የተለያዩ አትክልቶችን በመስኖ ለማልማት መሬታቸውን እያዘጋጁ መሆኑን ይናገራሉ።
በዞኑ ባለፈው ዓመት በተከናወነ ተመሳሳይ የበጋ መስኖ ልማት ከአምስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያሳያል።