ቀጥታ፡

በመደመር መንግሥት እሳቤ በመመራት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሕዝብን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ ይሰራል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3 /2019 (ኢዜአ)፦በመደመር መንግሥት እሳቤ በመመራት በቀጣዮቹ አምስት አመታት የሕዝብን ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት በላቀ መልኩ ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ አባላት ገለጹ፡፡

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ራዕይ

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደውን ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ፣ ብልፅግና ፓርቲ የሕዝብን ይሁንታ በማግኘት በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች ቀደም ብሎ እንዲሁም መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም አዲሱን የመደመር መንግሥት መመስረቱ ይታወቃል።

በየደረጃው በተካሄዱት የመደመር መንግሥት ምስረታ ጉባኤዎች አዲሶቹ የምክር ቤት አባላት፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የካቢኔ አባላት የሥራ ኃላፊነታቸውን በመረከብ በይፋ ሥራ ጀምረዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ተሿሚ የካቢኔ አባላትም፤ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሕዝብን አደራ በላቀ የኃላፊነት መንፈስ በመቀበል የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በመደመር መንግሥት እሳቤ በመመራት የመዲናዋን እድገት የሚያፋጥኑና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን በቁርጠኝነት እንደሚተገብሩ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ፤ ቢሮው በመደመር መንግሥት እሳቤ ሰላምንና ጸጥታን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

የከተማዋን ሰላም እና ጸጥታ ከማስጠበቅ ባለፈ፣ የዕቅዶቹን ውጤታማነት በዜጎች የዕለት ተዕለት እርካታ አንጻር እንደሚገመገምም ገልጸዋል።

የወንጀል መከላከል አቅምን ለማሳደግና የኅብረተሰቡን ደህንነት በብቃት ለመጠበቅ ሕዝብን በማሳተፍና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል፡፡

በመደመር መንግሥት እሳቤ መሠረት ዕቅዶቻችንን ከልሰን የሕዝብ ተጠቃሚነትና የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ማረጋገጥ ላይ በሰፊው እንሠራለን ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አያልነሽ ሐብተማርያም በበኩላቸው፤ የመደመር መንግሥት ዋናው መለኪያ የዜጎች እርካታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ሥራዎቻችን የሚገመገሙት ዜጎች ምን ያህል ተጠቃሚ ሆነዋል እንዲሁም በአገልግሎቶቻችን ምን ያህል እርካታ አግኝተዋል ከሚሉ መመዘኛዎች አንጻር ነው ሲሉ አመላክተዋል።

የሚሠሩት ሥራዎች በሙሉ ለብሔራዊ አቅምና ለኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽኑ ምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ በግራንድ ስትራቴጂው መሠረት ዕቅዶች መከለሳቸውን አስታውቀዋል።

ሥራዎች በዲጂታላይዜሽን ታግዘው በፍጥነት፣ በጥራት እና በተደራሽነት እንደሚፈጸሙም አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ፤ በመደመር መንግሥት እሳቤ እና አሠራር መሠረት የንግድ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና የቁጥጥር ሥራዎችን በዲጂታል ታግዞ ለማከናወን ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።

በንግድ ቢሮ የሚሰጡ አገልግሎቶች በሙሉ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት እንደሚሰጡና ዜጎችም በተሰጣቸው አገልግሎት እርካታቸውን የሚገልጹበት አሠራር መዘርጋቱንም አክለዋል።

በማኑዋል ይካሄድ የነበረው በር ለበር የቁጥጥር ሥራ አሁን ላይ ቅልጥፍናን በሚያስገኙ አዳዲስ የዲጂታል (ኢ-ፎርማት) ሥርዓቶች እንደሚታገዝም የቢሮ ኃላፊዋ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም