ቀጥታ፡

ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ- የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማረጋገጫ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3 /2019 (ኢዜአ)፦በቅርቡ ስራ የጀመረው ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ የዘርፉ ማዕከል የሚያደርግና ዓለም አቀፍ የንግድ ተወዳዳሪነቷን የሚያሳድግ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

የመደመር መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ከመሰረቱ ለማሻሻል በተገበረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች መካከል ማዕድን አንዱ ነው።

የማዕድን ዘርፉን በቴክኖሎጂ ታግዞ በማልማት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ እና ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል። 


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ መካከል በተደረገ አጋርነት በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባው ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም ስራ መጀመሩ ይታወቃል።

‎ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ይህ የማጣሪያ ፋብሪካ፤ በሀገር ውስጥ ምርት ላይ እሴት ለመጨመር፣ የኢትዮጵያን የማዕድን ዘርፍ ለማጠናከርና ኢትዮጵያን በውድ ማዕድናት ማጣሪያ ቀጣናዊ ማዕከል ለማድረግ ለተጀመረው ጉዞ ትልቅ ምዕራፍ ነው። 

‎ይህ ውጥን ሀብቶቻችንን ከኢንዱስትሪ አቅም ጋር በማስተሳሰር ወጭ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ የሰለጠነ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የጌጣጌጥ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ፣ እንዲሁም ይበልጥ ግልጽ እና ተወዳዳሪ የሆነ የወርቅ እሴት ሰንሰለት ለመገንባት የመደመር መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል። 

‎ከማዕድን ማውጣት እስከ ኢንዱስትሪ ሽግግር ድረስ የላቀ እሴት እየተፈጠረ መሆኑንና ፋብሪካው በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማንጠር አቅም እንዳለውም ተናግረዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ የወጪ ንግድ ገቢን በማሳደግ የንግድ ሚዛንን የሚያሻሽል መሆኑን ገልጸዋል።


 

የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ብርሃኑ አለሙ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ያልተጣራ ማዕድን ወደ ውጭ ስትልክ በመቆየቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ያህል ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አላገኘችም።

ማጣሪያ ፋብሪካው ወርቅን ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናትን በሀገር ውስጥ በማጣራት እና በማቀነባበር በተሻለ ዋጋ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል። 

ፋብሪካው የተጣራና ጥራቱን የጠበቀ የማዕድን ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ የሚያሳድግ በመሆኑ የወጪ ምርት ዓይነት ሲጨምር የንግድ ሚዛንም እንደሚሻሻል ጠቁመዋል።

የምርት ጥራትን በመጨመር ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግና ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ማዕከል ማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

ፋብሪካው የሀገር ውስጥ የማዕድን አምራቾችን፣ አቅራቢዎችን፣  አገልግሎት ሰጪዎችንና  ጌጣጌጥ አምራቾችን ማገናኘት የሚያስችል ከመሆኑ ባሻገር የሥራ ዕድል ፈጠራንና የኢንዱስትሪ አቅምን ያሳድጋል ብለዋል።

ፋብሪካው ከጎረቤት ሀገራት የንግድ አጋሮች ጋር በጋራ ለመሥራትና ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ውጤታማነት እንደሚያሳይ ጠቁመው ከማዕድን ማውጣት እስከ ወጪ ንግድ ያለውን ሂደት በተቀናጀ ሥርዓት ለመምራት ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል። 

ፋብሪካው የማዕድን አምራቾች በሕጋዊ መንገድ ምርታቸውን እንዲሸጡ የሚያበረታታና ሕገወጥ ንግድንና ዝውውርን የሚቀንስ ነው ብለዋል።


 

በቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምድር እና ማዕድን ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሙስጠፋ መሐመድ በበኩላቸው ፤ የማዕድን ዘርፍ ላይ ትኩረት መደረጉን ገልጸው፤ ከፍተኛ ውጤትም እየተገኘበት ይገኛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ወርቅ፣ ታንታለምና ሌሎች ማዕድናትን ሳይቀነባበሩ ለውጭ ገበያ ታቀርብ እንደነበርና በዚህም የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ ሳትሆን መቆየቷን ገልጸዋል።

ስራ የጀመረው የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ የማዕድን ምርቶችን አጣርቶ ለዓለም ገበያ በማቅረብ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት እድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል።

ፋብሪካው ከዩኒቨርሲቲዎችና ከምርምር ተቋማት ጋር በሚኖረው የስራ ግንኙነት ለአቅም ግንባታ እንደሚያግዝ ተናግረው፤ ይህም ኢትዮጵያን በማዕድን ዘርፍ በምሥራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ያደርጋታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም