ቀጥታ፡

ቢሾፍቱ ከተማን የቱሪዝምና የኮንፍረንስ ማዕከል ለማድረግ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራትን ለማላቅ ትኩረት ተሰጥቷል 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3 /2019 (ኢዜአ)፦ቢሾፍቱ ከተማን ተመራጭ የቱሪዝምና የኮንፍረንስ መዳረሻ ለማድረግ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራትን ለማላቅ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን የከተማዋ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ራዕይ

በመደመር መንግሥት እሳቤ በመላ ሀገሪቱ እየተከናወነ ከሚገኘው የኮሪደር ልማት አማካኝነት ገጽታቸውን ካደሱ እና እያደሱ ካሉ ከተሞች መካከል ቢሾፍቱ ከተማ አንዷ ናት። 

የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ከተማዋ ያሏትን የመልማት ጸጋዎች በማልማት የቱሪስት መስህብነቷን የበለጠ በመግለጥ ላይ ይገኛል።

የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የቱሪስቶችን ቁጥር በመጨመር ለዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።


 

ከተማዋ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶች በማልማት፣ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን የበለጠ በማስፋፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማላቅ ትኩረት መደረጉንም አክለዋል።

የከተማዋን ሰባት የተፈጥሮ ሐይቆች፣ ምቹ የአየር ሁኔታና ያሉትን የሆቴልና የሪዞርት መሰረተ ልማቶች በመጠቀም የጎብኚዎችን ፍሰት ለማሳደግም ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል። 

በተለይም በሐይቆቹ ዙሪያ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችና ምቹ የመዝናኛ ስፍራዎችን መገንባት ለሚሹ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚያስችሉ በቂ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ከተማዋ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ማስተናገድ የሚያስችላትን መሰረተ ልማቶች በማሟላት በኩል ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው እነዚህ ተግባራት በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። 

ከተማዋ ያሏትን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ሀብቶች በማልማት ለቱሪዝም ፍሰት እና ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝም ከንቲባው አክለዋል።


 

በዚህም በሀርሰዴ ሐይቅ አካባቢ የኮንቬንሽን ማዕከልና የስብሰባ እንዲሁም ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ አዳራሾች መኖራቸው ለዚህ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል። 

ተጨማሪ ሆቴሎችን፣ ሪዞርቶችንና የመዝናኛ ስፍራዎችን በማስፋፋት የከተማዋን ቱሪስቶችን የማስተናገድ አቅም ለማሳደግ እንደሚሰራ ነው የተናገሩት።

በተጨማሪም በከተማዋ እየተገነባ ያለው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለከተማዋ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ትሩፋት መሆኑንና የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማሳደግ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም