አይኤምኤፍ ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚፈልግ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
አይኤምኤፍ ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚፈልግ ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2019 (ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር ያለውን የትብብር አድማስ ማስፋት እንደሚፈልግ አስታወቀ።
የ2026 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በታይላንድ ባንኮክ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከስብሰባው ጎን ለጎን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የፊሲካል ጉዳዮች ክፍል እና ከገንዘብና ካፒታል ገበያዎች የስራ ክፍል ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርጓል።
ከአይኤምፊ ፊስካል ጉዳዮች ዘርፍ ጋር በተካሄደው ውይይት፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር በሚደረጉ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
ድርጅቱ ለሚኒስቴሩ እየሰጠ የሚገኘውን የቴክኒክ ድጋፍ አፈጻጸም ተገምግሟል።
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሪፎርም አጀንዳዎች መሠረት በቀጣይ ተጨማሪ ድጋፍ የሚደረግባቸውን ዕድሎችና የትብብር መስኮች ላይ ምክክር ተደርጓል።
በተያያዘም፣ ከተቋሙ የገንዘብና ካፒታል ገበያዎች የስራ ክፍል ጋር በተካሄደው ውይይት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚሰጡ የአቅም ግንባታ ድጋፎች ላይ ያተኮረ ነው።
ውይይቱ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በኩል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየተደረገ ያለውን የቴክኒክ ድጋፍ ያካተተ ነው።
የተቋሙን የማስፈጸም አቅም የበለጠ ለማጠናከርና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የጀመረውን የሪፎርም አጀንዳ ለማጠናከር የሚያስችሉ ተጨማሪ የድጋፍ መስኮችን የመለየት ሥራ ተከናውኗል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የተመራው ልዑክ ከስብሰባው ጎን ለጎን የተለያዩ ውይይቶችን እያደረገ ይገኛል።