የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ ጋር የመልስ ጨዋታውን ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ ጋር የመልስ ጨዋታውን ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3 /2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ማጣሪያ ሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ከሩዋንዳ ጋር ያካሂዳል።
ጨዋታው ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በድሬዳዋ ስታዲየም ይከናወናል።
ሁለቱ ሀገራት መስከረም 27 ቀን 2019 ዓ.ም በኪጋሊ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
የሩዋንዳዋ ኡዛዬሴንጋ ሊድያ በራሷ ላይ ግቡን አስቆጥራለች።
ውጤቱን ተከትሎ በቻለው ለሜቻ የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ እድሉን አስፍቷል።
ሉሲዎቹ ከመጀመሪያው ጨዋታ መልስ ወደ ድሬዳዋ በማቅናት ዝግጅቱን አድርጓል።
ብሔራዊ ቡድኑ ከጨዋታው በፊት የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በድሬዳዋ ስታዲየም አከናውኗል።
ቡድኑ በጥሩ ሞራል እና ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በአንድሬ ካሳ ሙቡንጎ የሚመራው የሩዋንዳ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምዱን ትናንት በድሬዳዋ ስታዲየም አድርጓል።
ሉሲዎቹ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፉ ሶስተኛውን ዙር የሚቀላቀሉ ሲሆን ከታንዛንያ እና ቦትስዋና አሸናፊ ጋር ይጫወታሉ።
በአምስት ዙሮች በሚካሄደው ማጣሪያ ሁለት ሀገራት አፍሪካን ወክለው በኦሊምፒክ ውድድሩ ላይ ይሳተፋሉ።
በአጠቃላይ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሴቶች እግር ኳስ 12 ሀገራት የሚሳተፉ ይሆናል።