በሶማሌ ክልል የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን የማስፋፋት ስራ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን የማስፋፋት ስራ እየተካሄደ ነው
ጅግጅጋ፣ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ)፦በሶማሌ ክልል የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን የማስፋፋት ስራ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ አስታወቁ።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ በክልሉ ሶስተኛ የሆነውን ጅግጅጋ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ማምሻውን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በሥነሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት መሶብ የአንድ ማዕከል ለህብረተሰቡ ቀልጣፋና ምቹ አገልግሎቶት ለመስጠት እያስቻለ ነው ።
በዚህም በወረዳዎችና በከተማ አስተዳድሮች ማእከላቱን በማስፋፋት የህብረተሰቡን ግዜና ወጪ ለመቀነስና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የጅግጅጋ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ሻፊ አህመድ በበኩላቸው በማዕከሉ 11 አገልግሎቶች እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
በማዕከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶች በዲጂታል የታገዙ መሆናቸውን ጠቁመው በዚህም የህብረተሰቡ ቀልጣፋና ምቹ አገልግሎት እንደሚያገኝ አስታውቀዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን በጅግጅጋ ከተማ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የተገጠሙ የደህንነት ካሜራዎች በይፋ ስራ ጀምረዋል ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በሺር አህመድ በከተማው የተተከሉ የደህንነት ካሜራዎች የህዝቡን ጸጥታና ሠላም ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
በተለይም ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል ለሚከናወኑ ተግባራት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥሩና የፖሊስን ስራ የሚያዘምኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።