ቀጥታ፡

የግል ዘርፍ ተቋማትን ማጠናከር የኢትዮጵያን የነገ ብልፅግና ማረጋገጥ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2019(ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገትና የወደፊት ብልፅግና የግል ዘርፉ ጠንካራ፣ ተወዳዳሪና ማኅበራዊ ኃላፊነቱን የሚወጣ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ሚድሮክ ለሀገር" በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደውን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የአውደ ርዕይ ሳምንት ከፍተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መንግሥት የግል ባለሀብቱን እና ማኅበረሰቡን በማበረታታት በፖሊሲዎችና ሕግጋት ማዕቀፍ ውስጥ ተሰማርተው እንዲሰሩ ድጋፍ ያደርጋል።

በዚህም የግል ባለሀብቱ መንግሥት ያልደረሰባቸውን ዘርፎች በመደገፍ፣ አዳዲስ ፈጠራዎችን በማስተዋወቅና ሀብት በማመንጨት ለሀገር ኢኮኖሚ የድርሻውን ያበረክታል ብለዋል።

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኢትዮጵያ የግል ዘርፍ ላለፉት 30 ዓመታት ልዩ አሻራ በማሳረፍ በንግድ ስኬቱ ብቻ ሳይሆን በሀገር ግንባታ ያበረከተውን አስተዋጽኦ በአብነት ጠቅሰዋል።

የአንድ ተቋም ታላቅነት የሚለካው በሚያገኘው ትርፍ፣ በሚያመርተው ምርት ወይም በሚሰጠው አገልግሎት ብቻ አለመሆኑን ገልጸዋል።

የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት፣ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በማቅረብና ታማኝ ግብር ከፋይ በመሆን ለሀገሪቷ ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በተለይም በፈተና ወቅት ከሀገርና ከሕዝብ ጎን መቆም የአንድን ተቋም እውነተኛ ዋጋ ይወስናል ብለዋል።

የተቋሙ ማኅበራዊ ተሳትፎ በቁጥር የሚገለጽ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን የሀገር ፍቅርን በተግባር የሚያሳይ መሆኑን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በለውጥ ጉዞ ላይ በምትገኝበት የሀገሪቷን የልማት ፍላጎት ለማሳካት የመንግሥት ጥረት ብቻ በቂ እንዳልሆነ ገልጸው፣ የግል ዘርፉ፣ ኢንቨስተሮች እና ሌሎችም ባለድርሻዎች የየራሳቸውን አስተዋጽኦ መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ተቋሙ የተጠቀመባቸውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና የሥራ ልምዶች በራሱ ብቻ ሳይገድብ፣ ለሌሎች የኢትዮጵያ ተቋማት የእውቀት ሽግግር ማድረግ እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።

ይህም የግል ዘርፉ የጋራ አቅም እንዲገነባና የሀገሪቷ ኢኮኖሚ ዘመናዊና ተወዳዳሪ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፤ ተቋሙ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርሙን መሠረት ያደረጉ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ቀጣይነት ያለው እድገት እያስመዘገበ ይገኛል።

የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ የሚያረጋግጡና አዳዲስ እምርታዎችን የሚያመጡ ስልታዊ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በትግበራ ላይ ይገኛልም ብለዋል።

ተቋሙ ሀገር ወዳድ እንደመሆኑ መጠን ያገኘውን፣ በሀገሩ ያፈራውን ሀብት መልሶ በሀገር ውስጥ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ እንደሚያውል ተናግረዋል።

ስለሆነም ዕድገታችንና ትርፋማነታችን የሚመሠረተው በኢትዮጵያ ዕድገት ላይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም