ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል አረንጓዴ ኢኮኖሚ እየገነባች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል አረንጓዴ ኢኮኖሚ እየገነባች ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2 /2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል አረንጓዴ ኢኮኖሚ እየገነባች መሆኗን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከ192 አባል ሀገራት የመጡ ሳይንቲስቶች፣ ውሳኔ ሰጪዎች፣ የሚቲዎሮሎጂ ባለሙያዎች እና የዘርፉ ተመራማሪዎች የተገኙበትንና ከጥቅምት 2 እስከ 6 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆየውን ዓለም አቀፍ ፎረም ማካሄድ ጀምሯል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም የሚያስችል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ አቅም እየገነባች ነው።
በዚህም መንግሥት የአየር ንብረት ተለዋዋጭነትን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን በመተግበር የታዳሽ ኃይል ምንጮችን እያስፋፋ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሀገሪቱን የደን ሽፋን ከ17 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደጉንም አመልክተዋል።
የዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ መንግሥታት አቀፍ ባለሙያዎች ፓናል ሰባተኛው የግምገማ ሪፖርት ውስጥ ለፖሊሲ አውጪዎች ተግባራዊ መፍትሔዎች እንዲቀርቡ፣ በታዳጊ ሀገራት ያሉ የመረጃ ክፍተቶች እንዲሞሉና የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን በትክክል ለመለየት እንዲረዳ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የሙቀት መጨመርና የዝናብ ሁኔታ መለዋወጥ እየተባባሱ ነው ብለዋል።
አህጉሪቱ ለዓለም አቀፍ የግሪንሃውስ ጋዝ ልቀት ያላት አስተዋጽኦ እጅግ አነስተኛ ቢሆንም፤ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች ግን ከፍተኛ ተጋላጭ መሆኗን አስረድተዋል።
ለዚህም የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን፣ የአየር ንብረት መረጃ አገልግሎቶችን፣ የምልከታ መረቦችንና የምርምር አቅሞችን ማሳደግ የሕብረተሰቡን ሕይወት ለመታደግና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በኢንስቲትዩቱ አማካይነት የአየር ሁኔታና የአየር ንብረት ምልከታ መረቦችን በማስፋፋት፣ የትንበያ አገልግሎቶችን በማሻሻል እንዲሁም የአየር ንብረት ምርምርን በመደገፍ ለቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ትብብሮች የላቀ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን ጠቁመዋል።
የዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ መንግሥታት አቀፍ ባለሙያዎች ፓናል ሪፖርቶች ለመንግሥታት፣ ለተመራማሪዎችና ለልማት አጋሮች የአየር ንብረት ስጋቶችን በትክክል ለመረዳትና ውጤታማ ምላሾችን ለማዘጋጀት ጠቃሚ መሠረት እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
በሰባተኛው የግምገማ ዙር የሚካሄዱ ውይይቶች ሳይንሳዊ ግኝቶችን ለፖሊሲ አውጪዎችና ለማኅበረሰቡ የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዙ ተናግረዋል።