የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የትውልዱ የጋራ ጥያቄና ሀገራዊ አጀንዳችን ነው - የፓርቲ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የትውልዱ የጋራ ጥያቄና ሀገራዊ አጀንዳችን ነው - የፓርቲ አመራሮች
አዳማ፣ ጥቅምት 02/2019 (ኢዜአ) ፦ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የትውልዱ የጋራ ጥያቄና ሀገራዊ አጀንዳችን ነው ሲሉ የተለያዩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ተናገሩ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ፣ ታላቅ ርእይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የባሕር በር ጉዳይን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና መቀጠል አትችልም ማለታቸው ይታወሳል።
በመሆኑም የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑ የሚታወቅ ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የትውልዱ የጋራ ጥያቄና ሀገራዊ አጀንዳችን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር በየነ ደሳለኝ፤ ኢትዮጵያ የባህር በሯን ያጣችበት መንገድ የሁላችንም ቁጭት በመሆኑ ወደ ቀደመ ባለቤትነቷ እንድትመለስ እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነቷን በማይታወቅ መልኩ ድንገት ያጣችው ቢሆንም ታሪክን፣ ህጋዊነትንና ቅርበትን መሰረት በማድረግ በዚህ ትውልድ ይመለሳል ብለዋል ።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባለፈም የሉአላዊነቷና የህልውናዋ መሰረት መሆኑን ገልጸው ጥያቄውም ምላሽ ማግኘት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
በተለይ በቀጣናው ያለውን አሁናዊ የኃይል አሰላለፍ ለመዋጀት እና ብሔራዊ ደህንነትን ለማስጠበቅ የባሕር በር ጥቅሙ ምትክ የለሽ እንደሆነ አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር የመንግስት ምስረታ ላይ ባደረጉት ንግግር የባህር በር ባለቤትነት በሰጥቶ መቀበል መርህ እንዲመለስ እንደሚሰራ ማንሳታቸውን አስታውሰው የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲም በቅርበት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) የማእከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ሀብታሙ ተሰማ፤ የባሕር በር ተጠቃሚነት የተሳለጠ የንግድ ሥርዓት ለመዘርጋት እና ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ለተፈጻሚነቱ ሁላችንም እንረባረባለን ብለዋል።
የባሕር በር ባለቤትነት መብትን ለማረጋገጥ የመደመር መንግሥት በሰጥቶ መቀበል የዲፕሎማሲ መርህ መስራቱ ሊደነቅ የሚገባው ስለመሆኑም አንስተዋል።
የአዲስ ትውልድ ፓርቲ አባል ወጣት ቦንቱ አብርሃም፤ የባሕር በር ጉዳይ የዜጎች ቁጭትና ለዓመታት ሲብሰለሰል የቆየ ጥያቄ በመሆኑ በዚህ ትውልድ ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላት ገልፃለች።
የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብ የጋራ ጥያቄና ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑን አንስታ በጉዳዩ ላይ የመንግስትን የዲፕሎማሲ ጥረት አድንቃ ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ጠንካራ አቋም ይዘን እንሰራለን ብላለች።