በድሬደዋ አስተዳደር የትምህርት ቤቶች የምገባ መርሃ ግብርን በቅንጅት በመተግበር የትምህርት ጥራትን ለማሳካት ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬደዋ አስተዳደር የትምህርት ቤቶች የምገባ መርሃ ግብርን በቅንጅት በመተግበር የትምህርት ጥራትን ለማሳካት ትኩረት ተደርጓል
ድሬደዋ፣ ጥቅምት 2/2019(ኢዜአ)፡- በድሬደዋ አስተዳደር የትምህርት ቤቶች የምገባ መርሃ ግብርን በቅንጅት በመተግበር የትምህርት ጥራትን ለማሳካት ትኩረት መሰጠቱን ከንቲባ አብዱላሂ አደን ገለፁ።
ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር እና ብዙአየሁ ታደለና ቤተሰቦቹ ፋውንዴሽን ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የምግብ ቁሳቁሶች ለአስተዳደሩ የትምህርት ቤቶች ምገባ መርሐ ግብር ድጋፍ አድርገዋል።
ለትምህርት ቤቶች ምገባ መርሐ ግብር የተደረገውን ድጋፍ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አብዱላሂ አደን እና የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ ተረክበዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አብዱላሂ አደን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ አስተዳደሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በትምህርት ቤቶች የምገባ መርሐ ግብር፣ በትምህርት ግብዓት ማሟላት እና በሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።
ከእነዚህ ተግባራት መካከል በናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር እና በብዙአየሁ ታደለና ቤተሰቦቹ ፋውንዴሽን የተደረገው ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የምግብ ቁሳቁሶች ድጋፍ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
በትምህርት ቤቶች የሚካሄደው የምገባ መርሐ ግብር የተማሪዎችን የትምህርት ማቋረጥ መቀነሱንና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
መርሐ ግብሩን ለማሳካት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሠራቱን አንስተው፤ የብዙአየሁ ታደለና ቤተሰቦቹ ፋውንዴሽን እንዲሁም ናሽናል ሲሚንቶ እያደረጉት የሚገኘው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ በበኩላቸው፤ አስተዳደሩ የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ለማሳደግ ባለሀብቶችንና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የምገባ መርሐ ግብር ሲያካሂድ መቆየቱን አስረድተዋል።
የዚሁ አካል ሆኖ ዛሬ ከተደረጉት የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ መካከል የተለያዩ የዱቄት፣ የዘይት፣ የጨው፣ የስኳር፣ የሩዝ፣ የፓስታ እና የማካሮኒ ምርቶች ይገኙበታል ብለዋል።
የተደረገው የምግብ ድጋፍም በ8 ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ከ4 ሺህ በላይ ተማሪዎች ፍጆታ የሚውል መሆኑን ተናግረዋል።
የፋውንዴሽኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ገድፍ፤ ፋውንዴሽኑ በአካባቢ ጥበቃ፣ በጤናና በትምህርት ዘርፎች ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዛሬው ዕለትም ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የምግብ ቁሳቁሶች ለተማሪዎች ምገባ መደገፋቸውን ገልጸው፣ ፋውንዴሽኑ ተመሳሳይ ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።