የጣና ፎረም ሂደቱና ውጤቱ - ኢዜአ አማርኛ
የጣና ፎረም ሂደቱና ውጤቱ
የጣና ፎረም ሂደቱና ውጤቱ ምን ይመስላል?
የአፍሪካ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራንና ሌሎችንም በአንድ መድረክ በማሰባሰብ እንዲመክሩ በማሰብ የተቋቋመው ጣና ፎረም ለአህጉራዊ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሁም ለጠንካራ የትብብር ግንኙነት ወሳኝ መድረክ ሆኗል።
በዚህም የጣና ፎረም ላለፉት አስራ አንድ ተከታታይ አመታት ተካሂዶ ዘንድሮም 12ኛው መድረክ በውቢቷ ባህር ዳር ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለታል። በአፍሪካ ግጭትን መከላከል፣ ለችግሮች የጋራ መፍትሄ ማበጀት ላይ የሚያተኩረው መድረክ አፍሪካ ችግሮቿን በራሷ አቅም ለመፍታት የሚያስችል ጠንካራ ትብብር በመፍጠር ለተግባራዊነቱ ለመትጋት የሚያስችል ነው።
በመሆኑም በየአመቱ የሚካሄደው የጣና ፎረም ዓላማ በአፍሪካ የሰላም ፖሊሲዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር፣ የአህጉሪቱን ድምፅ ማጠናከር፣ የክልላዊ ትብብርን ማሳደግና የሚነሱ ሀሳቦች ወደ ተጨባጭ ውጤት እንዲሸጋገሩ ማድረግ ይሆናል። በዚሁ መሰረትም የዘንድሮው የጣና ፎረም “በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፡ የኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትና የጂኦፖለቲካ ለውጥ” የሚል መሪ ሃሳብ በማንገብ በጣና ሀይቅ ዳርቻ ከጥቅምት 13 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም ይካሄዳል።
ከ250 በላይ እንግዶች በሚታደሙበት ፎረም ላይ የተለያዩ አገራት መሪዎች፣ የተቋማት ሃላፊዎች፣ የቀድሞ መሪዎች የሚገኙ ሲሆን ለጉባኤው መሳካትም ኢትዮጵያ የተሟላ ዝግጅት ማድረጓ ታውቋል።
በአህጉሪቷ የሚስተዋሉ ግጭቶችን መከላከል፣ ሰላምና ደኅንነትም ማስጠበቅ እንዲሁም ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነትን ማጠናከር ይሆናል። በተለይም በአገራት መካከል በቀጥታ፣ በግልጽና በጥልቀት የውይይት አውዶችን በማስፋት በጋራ መስራትን የሚያበረታታ ነው።
በፎረሙ ላይ የሚነሱ ጥልቅ ትንታኔዎችና የተለያዩ ምክረ ሐሳቦች ለፖሊሲ ግብአት፣ ለተቋማዊ ለውጥና ለተግባት ተኮር እንቅስቃሴዎች ጉልህ ፋይዳ የሚኖረው መሆኑ ይታመናል።
አፍሪካ በዓለም አቀፍ የሰላም፣ የደኅንነትና የፖለቲካ መድረኮች ላይ በሚኖራት ተሳትፎ የተደራጀና የተቀናጀ አቋም በመያዝ ለመቅረብ ጣና ፎረም ወሳኝ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። የጣና ፎረም የግጭት መፍትሔ አስፈጻሚ ተቋም ባይሆንም፣ ውሳኔ ሰጪዎች አዲስ አቅጣጫ እንዲያዩ፣ የጋራ ግንዛቤ እንዲፈጥሩና ለቀጣይ እርምጃዎች መሠረት እንዲያኖሩ የሚያግዝ መሆኑም ይታመናል።
የጣና ፎረም ያለፉት 11 መድርኮች የአፍሪካ የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ በመምከር የመፍትሄ አመላካች ሃሳቦች የሚነሱበት ስለመሆኑ መናገር ይቻላል። በመድረኮቹ ከአፍሪካ የውስጥ ግጭቶችና የሰላም ግንባታ እስከ ክልላዊ ትብብር፣ የዓለም የኃይል ሚዛን፣ የኢኮኖሚ ልማትና የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጥቅሞችና ተፅእኖዎቻቸው ላይ የጋራ ግንዛቤ የመያዝ እድል ተፈጥሯል። የሰላምን ጉዳይ ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከአስተዳደርና ከዓለም አቀፍ ግንኙነት ጋር አስተሳስሮ በማየት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተመላክተውበታል።
የ11ኛው ጣና ፎረም፣ “አፍሪካ በለውጥ ላይ ባለ የዓለም ሥርዓት” (Africa in an Evolving Global Order) በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድ የአገራት መሪዎች፣ ቀድሞ መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮችና ሌሎችም ታድመውበት በስኬት ተከናውኗል።
በፎረሙ ከተነሱት አበይት ጉዳዮች መካከልም በአፍሪካ ሕብረት፣ በኢጋድ እና በተባበሩት መንግሥታት መካከል የሰላምና ደኅንነት ቅንጅትን የማጠናከር። በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት እንዲሁም እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥና የዘመኑ ክስተትና በፍጥነት እየደገ የመጣው ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ላይ ያተኮረ ነበር። በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስትሪና በኃይል ልማትና ቀጣናዊ ትስስርን በተመለከተም በስፋት ተመክሮበታል።
በመሆኑም የጣና ፎረም የውይይትና የፖሊሲ ሐሳቦች ማፍለቂያ እንዲሁም የምክረ ሐሳብና መፍትሄዎች ማመላከቻ መድርክ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። የአፍሪካ መሪዎች፣ ምሁራን፣ ዲፕሎማቶችና የተለያዩ የፖለቲካና ማህበራዊ እንዲሁም የንግድ ተቋማት ተወካዮች የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮችን በቀጥታ የሚወያዩበት የተለመደ መድረክም ሆኗል።
የፎረሙ ዋና ስኬትም በአህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት ላይ የታዩ መሻሻሎች፣ የተፈቱ ችግሮችና የተተገበሩ ፖሊሲዎችን መጥቀስ ይቻላል።
በ2026 ከጥቅምት 23 እስከ 25 በባሕር ዳር የሚካሄደው 12ኛው ጣና ፎረም፣ “በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፡ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦፖለቲካ ለውጥ” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ይሆናል። የዘንድሮው መሪ ሃሳብ የሚያመለክተውም ለዘላቂ ሰላም የኢኮኖሚያዊ ልእልና ፣ የሀብት አጠቃቀም፣ የኢንዱስትሪ አቅምና ሌሎችንም ያካተተ ነው።
ከፎረሙ የሚጠበቁ አበይት ነጥቦች መካከልም አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቷንና የዲጂታል አቅሟን ለራሷ ልማትና ለዜጎቿ ጥቅም እንዴት ማዋል ትችላለች? የዓለም የኃይል ሚዛን እየተቀያየረ ባለበት ሁኔታ አፍሪካ የጋራ ፍላጎቷን እንዴት ማስጠበቅ ትችላለች? የሥራ ዕድል፣ የኢንዱስትሪ እድገት፣ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ውህደትን በተመለከተ የሚነሱ ጣቀሚ ሃሳቦች እንደሚኖሩ ይጠበቃል። የአገራት የንግድ፣ የመሠረተ ልማት፣ የሃይል ልማት ትስስርን ማጠናከርም ሌላው ትኩረት ይሆናል።