ቀጥታ፡

ጠመንጃ የሚያስነሳና ጫካ የሚያስገባ ምንም አይነት ምክንያት የለም - የቀድሞ ታጣቂዎች

ገንዳውኃ፣ ጥቅምት 02/2019ዓ/ም (ኢዜአ) ፦ ጠመንጃ የሚያስነሳና ጫካ የሚያስገባ ምንም አይነት ምክንያት የሌለ መሆኑን በመረዳት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለን መጥተናል ሲሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች ገለጹ።

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በጫካ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላምን ጥሪ በመቀበል መጥተዋል።

‎የቀድሞ ታጣቂዎቹ በተሳሳተ መንገድ ወደ ጫካ በመግባት በአካባቢው ህዝብ ላይ በፈፀሙት በደል መጸጸታቸውን ተናግረዋል።


 

ከታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ተልእኮ በመቀበል ጉዳት አድርሰናል፤ በደልም ፈፅመናል ያሉት የቀድሞ ታጣቂዎቹ በድርጊታቸው መጸጸታቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ጊዜ ጠመንጃ የሚያስነሳና ጫካ የሚያስገባ ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለ በአግባቡ ተገንዘበናል በማለት ለፈፀሙት ጥፋት ይቅርታቸውን ጠይቀዋል።

በመሆኑም በቀጣይ የልማት አርበኛና የሰላም አምባሳደር በመሆን የበደልነውን ህዝብ ለመካስ በመዘጋጀት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለን መጥተናል ብለዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረሰ አዱኛ፤ በጥፋታቸው ተጸጽተው የሰላምን እድል በመጠቀም የመጡ የቀድሞ ታጣቂዎችን አመስግነዋል።


 

በዞኑ አሁንም በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሰላምን ጥሪ ተቀብለው እንዲመጡ ጥሪ በማቅረብ ለመጡት አስፈላጊው ድጋፍና እገዛ የሚደረግ መሆኑን ገልጸው በልማት ህዝብን መካስ እንዲዘጋጁ አስገንዝበዋል።

የመተማ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ምክትል ኃላፊ አቶ አስፋው ውበት፤ የሰላምን ጥሪ ተቀብለው የመጡትን በማመስገን በጫካ የቀሩ ሌሎች ታጣቂዎችም ይህንኑ እድል እንዲጠቀሙ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም