የግል ዘርፉ መዋቅራዊ ሽግግርን በሚያሣልጡ ዘርፎች ላይ እንዲሠማራ ማበረታታትና መደገፍ አንዱ የመደመር መንግሥት ተግባር ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የግል ዘርፉ መዋቅራዊ ሽግግርን በሚያሣልጡ ዘርፎች ላይ እንዲሠማራ ማበረታታትና መደገፍ አንዱ የመደመር መንግሥት ተግባር ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ)፦ የግል ዘርፉ መዋቅራዊ ሽግግርን በሚያሣልጡ ዘርፎች ላይ እንዲሠማራ ማበረታታትና መደገፍ አንዱ የመደመር መንግሥት ተግባር መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ ብልጽግና በጠንካራ የመንግሥትና የግሉ አጋርነት ይገነባል ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ እውነተኛ አጋርነት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚድሮክ ዐውደ ርዕይ ሳምንትን ዛሬ ማስጀመራቸውን ጠቁመዋል።
እንደ ሚድሮክ ያሉ ጠንካራ ሀገር በቀል ተቋማትን ማበረታታትና ዐቅማቸውን ማሳደግ ማለት የሀገርን ምርታማነት ማሳደግ፣ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬና የግብር ገቢን ማሳደግ እንዲሁም የፈጠራና የቴክኖሎጂ ኀቅምን ማጠናከር መሆኑንም ነው የገለጹት።
ሚድሮክ ከትናንት ስኬቶቹ ባሻገር፣ የነገዋን ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራ፣ በምርታማነትና በወጪ ምርት እንዲገነባ ጭምር ነው ብለዋል።
የተቋሙ ልምድና ዘመናዊ አሠራሮች ለሌሎች ሀገር በቀል ተቋማት ሲተላለፉ፣ የአንዱ ስኬት የብዙዎች የዕድገት መሠረት እንደሚሆን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብልጽግና በመንግሥት ጥረት ብቻ አይረጋገጥም፤ በግሉ ዘርፍ እና በማኅበረሰቡ ጥረት ጭምር እንጂ ሲሉም ገልጸዋል።
በመንግሥት፣ በማኅበረሰቡና በግሉ ዘርፍ ጠንካራ አጋርነት፣ በጋራ ዐቅምና በጋራ ስኬት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት እናረጋግጣለን ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።