ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያዊነት፣ የድል አድራጊነትና የብሔራዊ ኩራት አርማና ቀለም ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያዊነት፣ የድል አድራጊነትና የብሔራዊ ኩራት አርማና ቀለም ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ)፦ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያዊነት፣ የድል አድራጊነትና የብሔራዊ ኩራት አርማና ቀለም መሆኑን የአባት አርበኞችና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
19ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ ተከብሯል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሕመድ ሽዴ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚልና አባት አርበኞችም ተገኝተዋል።
የመቶ አራት ዓመት የዕድሜ ባለጸጋና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በተለያዩ አውደ ውጊያዎች የተፋለሙት አባት አርበኛ መቶ አለቃ መኮንን መሸሻ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያውያን መለያ ነው።
ለኢትዮጵያ ዳር ድንበርና ለሰንደቅ ዓላማዋ ክብር ከደጃዝማች ገረሱ ዱኬ ጋር ጠላትን የተፋለሙት አባት አርበኛ መኮንን መሸሻ ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ መከበሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከዚህ መድረስ ውድ ዋጋ መከፈሉን ገልጸው፤ ወጣቱ በዕውቀትና ፈጠራ ታግዞ የአባቶቹን አደራ ማስቀጠል አለበት ብለዋል።
የአርበኛ ልጅ የሆኑት አርበኛ አስማማው መከተ ሰንደቅ ዓላማ ታላቅ ክብር፣ አርማ፣ ዓላማት የወደፊት አቅጣጫ ቀያሽ መሆኑን ገልጸዋል።
ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ የወቅቱ ወጣቶች የዛሬ አባት አርበኞች ሰንደቅ ዓላማቸውን በአንገታቸው ላይ ጠምጥመው ጠላትን ድባቅ መትተውታል ብለዋል።
በመሆኑም ወጣቶች ለኢትዮጵያና ሰንደቅ ዓላማዋ ክብር ሰጥተው ከዚህ ያደረሷትን ሀገር ለቀጣይ ትውልድ በክብር ማስረከብ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ተተኪ አርበኛና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ትዕግስት ሀይሌ፤ ሰንደቅ ዓላማ የክብር፣ አንድነትና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።
"ሰንደቅ ዓላማዬ የክብሬ መገለጫ ማንነቴ ነው" የሚሉት ተተኪ አርበኛ ትዕግስት፤ ወጣቶች በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርተው ለሀገራቸው ታሪክ መሥራት አለባቸው ብለዋል።
አባት አርበኛ መቶ አለቃ ጉደታ ገልሜሳ በበኩላቸው፤ ባንዲራ ማለት ቤታችንና ህልውናችን በመሆኑ የደስታዬ ምንጭ ነው በማለት ይገልጻሉ።
አሁንም ለባንዲራዬ ቀድሜ ራሴን እሰዋላታለሁ" የሚሉት መቶ አለቃ ጉደታ፤ የልጅ ልጆቻችን ባንዲራችሁ ማለት ቤታችሁ ሀገራችሁ መሆኑን ተረድታችሁ ሰላማዊ ትግልን ምርጫችሁ አድርጉ ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ራማታላ ሙሳ ቶላ፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሕብረ ብሔራዊነቷ መገለጫ፣ የሉዓላዊነቷ መከበሪያ አርማ መሆኑን ገልጸዋል።
ሰንደቅ ዓላማ ከቀለሙ በላይ የነጻነት፣ የታሪክና የአንድነትና የጋራ ተስፋችን ምልክት መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያውያን ደምና አጥንት የተገበረበት ነው ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ነጠላ ትርክትን በማስወገድና የወል ትርክት በመገንባት ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ማጠናከርና የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።