የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር የተሰጠንን ሀገራዊ ተልዕኮ በመወጣት ብሔራዊ አንድነትና መግባባትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል ቃል በመግባት ነው - የኢዜአ አመራሮችና ሠራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር የተሰጠንን ሀገራዊ ተልዕኮ በመወጣት ብሔራዊ አንድነትና መግባባትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል ቃል በመግባት ነው - የኢዜአ አመራሮችና ሠራተኞች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ)፦ የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር የተሰጠንን ሀገራዊ ተልዕኮ በመወጣት ብሔራዊ አንድነትና መግባባትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል ቃል በመግባት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) አመራሮችና ሠራተኞች ገለጹ።
19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሃሳብ በመላ ሀገሪቱ ተከብሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞችም የብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማ ቀንን በፓናል ውይይት እና በሠንደቅ ዓላማ መስቀል ሥነ-ስርዓት አክብረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ወቅት፤ የብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማ ዘርፈ ብዙ ትርጉም ያዘለ የሀገር ምልክት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማም የሀገርን ህልውና የማስቀጠል፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የመጠበቅና የዜግነት ፍቅርን የማጠናከር ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነትን ያዘለ ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የሚጠበቅብንን በመወጣት ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፋትን ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በትጋት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ዘርፉ ሀገራዊ መግባባትንና የሕዝቦችን አንድነት የሚያጠናክሩ መረጃዎችን በተገቢው ቅኝትና ቅርጽ በመፍጠር የዜግነት ፍቅርን ማጎልበት እንደሚገባ አክለዋል።
ለዚህም የዓድዋን መንፈስ በመላበስ የጋራ ጥረቶችን በማስተባበር የተሻለች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ሁልጊዜም በትጋት መስራት እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢዜአ አመራርና ሠራተኞችም የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር የተሰጠንን ሀገራዊ ተልዕኮ በመወጣት ብሔራዊ አንድነትና መግባባትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል ቃል በመግበት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢዜአ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነጋሲ አምባዬ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ አንድነትን ለመፍጠር አሰባሳቢ ትርክቶችን ወደፊት በማምጣት እንደ ተቋም መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ኢዜአ የሚያከናውናቸውን ዜና እና ዜና ነክ ተግባራት በማላቅ ሀገራዊ መግባባትና አንድነትን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራ የገለጹት ደግሞ የኢዜአ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ ናችው።
የኢዜአ የምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቤተልሄም አበባው በበኩላቸው ሠንደቅ ዓላማችን የአንድነታችን መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ለአፍሪካውያን የነጻነት ተምሳሌት መሆኑን ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ አመራርና ሠራተኞች በሰጡት አስተያየት፤ የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር የተሰጠንን ሀገራዊ ተልዕኮ በመወጣት ብሔራዊ አንድነትና መግባባትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል ቃል የምንገባበት ነው ብለዋል።
ሠንደቅ ዓላማን በምናከብርበት ጊዜ የተሰጠንን ሀገራዊ ኃላፊነት በመወጣት እና ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በትኩረት በመስራት የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።