ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ አስተማማኝ የሳይበር ምህዳር መገንባት ወሳኝ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ አስተማማኝ የሳይበር ምህዳር መገንባት ወሳኝ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ)፦ የዜጎችን ዲጂታል ደኅንነት እና ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ አስተማማኝ የሳይበር ምህዳር መገንባት ወሳኝ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ንቁ ዜጋ ደኅንነቷ ለተጠበቀ ሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ ከጥቅምት 01 እስከ 30 ቀን 2019 ዓ.ም የሚከበረውን ሰባተኛውን ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ወር በይፋ አስጀምረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን ዲጂታል ሽግግር በማፋጠን፣ የቴክኖሎጂ አቅሟን በማጠናከርና የዜጎችን ዲጂታል ደኅንነት እና ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ንቁ ዜጋ መፍጠርና አስተማማኝ የሳይበር ምህዳር መገንባት ወሳኝ ነው።
በዘመናችን የቴክኖሎጂ እድገት የሀገራትን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ እድገት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚወስን ዋነኛ መሳሪያ መሆኑን አንስተዋል።
ስለሆነም ኢትዮጵያም በዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ መድረክ ተወዳዳሪ ለመሆን ለዘርፉ ስትራቴጂያዊ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኑን ገልጸዋል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ የጥልቅ ዳታ ትንተና፣ ክላውድ ኮምፒውቲንግ፣ ኳንተም ኮምፒውቲንግና ዘመናዊ የቴሌኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማቶች የዓለምን ኢኮኖሚና የአስተዳደር ሥርዓት እየቀየሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ የፈጠራ አቅምን ማሳደግና ፈጣን የመዋቅር ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ሀገሪቱን ወደ ዘመናዊ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ጠንካራ መሠረት መጣሉን ጠቅሰው፤ በኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር እድገት፣ በቴሌኮም ዘርፍ የውድድር እድል መስፋፋት፣ በዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች መጎልበትና የመንግሥት አገልግሎቶችን በኦንላይን ማድረስ ረገድ የተገኙ ውጤቶች ለቀጣዩ ምዕራፍ መሠረት መሆናቸውን አንስተዋል።
አሁን የሀገሪቷን የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ አቅጣጫ የሚወስነው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስኬታማ እንዲሆን አስተማማኝ የሳይበር ደኅንነት መኖር የግድ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ80 በመቶ በላይ የሳይበር ጥቃቶች ከሰዎች የግንዛቤ እጥረት፣ ከግዴለሽነትና ከስህተት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ይህም የሰው ልጅ ንቃተ ሕሊናና ዝግጁነት ከቴክኖሎጂ መፍትሔዎች ጋር ተደምሮ የሳይበር ደኅንነት ዋነኛ መከላከያ መሆኑን ያመለክታል ብለዋል።
በመሆኑም ዜጎች በስልካቸው፣ በኮምፒውተራቸውና በሥራ ቦታቸው የሚያደርጉት ጥንቃቄ ለሀገራዊ የሳይበር ደኅንነት መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል።
መንግሥት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ውስጥ የሕፃናትን የኦንላይን ጥበቃ በማካተት ሀገራዊ የፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲዘረጋ አቅጣጫ ማስቀመጡንም ተናግረዋል።
በ2016 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በጸደቀው ሀገራዊ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲ የሕፃናትን የኦንላይን መብት የሚጠብቁና ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሚያግዙ አቅጣጫዎች መካተታቸውን ገልጸዋል።
ጠንካራ፣ አስተማማኝና ደኅንነቱ የተጠበቀ የሳይበር ምህዳር መገንባት የሁሉም ዜጋ ሀገራዊ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ በበኩላቸው፤ የሳይበር ጥቃቶች መጠንና ውስብስብነት እየጨመረ በመምጣቱ በግለሰቦች፣ በተቋማትና በሀገራዊ መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ስጋት እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።
በኢትዮጵያም በ2018 ዓ.ም ብቻ ከ71 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ሪፖርት መደረጋቸውን ገልጸዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የሀገሪቱን ዲጂታል ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በአሠራር ሥርዓት ዘርፎች ሰፊ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑም አስረድተዋል።
በተለይም በቅርቡ የጸደቀው የቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደኅንነት አዋጅ ባንኮችን፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና የኃይል ተቋማትን ጨምሮ ወሳኝ ተቋማት የሚያጋጥሟቸውን የሳይበር ስጋቶች ለመከላከልና አገልግሎታቸው ሳይቋረጥ እንዲቀጥል የሚያስችል አቅም ለመገንባት የሚያግዝ ነው ብለዋል።