ቀጥታ፡

ሠንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያውያን ልብ የታተመ የነፃነትና የአሸናፊነት ምልክት ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ):- ሠንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያውያን ልብ የታተመ የነፃነትና የአሸናፊነት ምልክት፣ የብሔራዊ ስሜት መገለጫ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ፡፡

19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን "ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተከብሯል፡፡

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሠንደቅ ዓላማ ቀን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ያለውን ፍቅር፣ ክብርና ቃል ኪዳን በልቡ የሚያድስበት ብሔራዊ ሁነት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ኅብረት ማሳያ፣ ሀገራዊ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት መገለጫ፣ ታሪካዊና ማኅበራዊ ትስስርና ሥነ ልቡናዊ አንድነት ማጽኛ ምልክት መሆኑን ተናግረዋል።

ሠንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያውያን ልብ የታተመ የነፃነትና የአሸናፊነት ምልክት፣ የብሔራዊ ስሜት መገለጫና ሥነ ልቡናዊ አንድነት ማፅኛ ነው ብለዋል።

የመስዋዕትነት፣ የነጻነት፣ የልዕልና እና የግዛት አንድነት ምልክት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የነገውን ብሩህ ተስፋ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።


የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ከሀገረ መንግሥት ምስረታ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ገልጸው፤ የዘንድሮው 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት በማጠናቀቅ የሕዝብ አደራ የተቀበለ አዲስ መንግሥት የተመሰረተበት ዓመት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

በየዘመናቱ ሀገር ለመውረር አሰፍስፈው የሚመጡ የውጭ ጠላቶችን የመመለስ ታሪክ አለን ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ አዲሱ መንግሥት የሠንደቅ ዓላማውን ክብርና ልዕልና የሚመጠን አቅልግሎት እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የብዙ አፍሪካውያን የእኩልነትና የነፃነት ተምሳሌት መሆኑን ገልጸው፤ ነጻነቷንና ልዕልናዋን አስጠብቃ ታፍራና ተከብራ የኖረች ታላቅ ሀገር ናት ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን የብዝኃነትን ውበት በማክበር፣ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሃሳቦች ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ሰላም፣ ጠንካራ ኢኮኖሚና ዘመናዊ ሥርዓተ መንግሥት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

መንግሥት ሰላምን ለማጽናትና ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር ሁልጊዜም ቁርጠኛ አቋም አለው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የኢትዮጵያን ዘመናዊ የፖለቲካ ፍኖት ኢትዮጵያን በሚገልጽ መልኩ ማዘመንና አጥብቆ መያዝ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንገድ ቀጣይነትና በጎነት ያለው ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ፤ ዘመኑን በዚህ መንፈስ ለማጽናት የወሰነ ትውልድ መፈጠሩን ገልጸዋል።

ይሄውም ኢትዮጵያ በቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትና ትብብር ላይ የተመሠረተውን ፍትሐዊ የባሕር በር የማግኘትና የመጠቀም መብት ያረጋግጣል ብለዋል።


ፕሬዝዳንቱ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለፌዴራልና ለክልል ፖሊስ እና ለመላው የፀጥታ ኃይሎች አባላት በኢትዮጵያ፣ በመንግሥትና በሕዝቦቿ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና መላው የፀጥታ ኃይሎች የሀገር አለኝታ፣ የሕዝብ ደኅንነት ዋስትና እና የሉዓላዊነት ካስማዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለሠንደቅ ዓላማቸው ሲሉ በበረሃና በዱር ሌት ከቀን ሳይሰለቹ ሀገርን ከውስጥና ከውጭ አደጋ ለመጠበቅ መስዋዕትነት የሚከፍሉት በትውልዱ ዘንድ ክብርና ሞገስ ያገኛሉ ብለዋል።

ቀደምት ትውልዶች የሀገራቸውን ሠንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ነፃነታቸውን እንዳስከበሩ ሁሉ፣ የዛሬው አደራ ተቀባይ ትውልድም ብሔራዊ አንድነቱንና መግባባቱን አጽንቶ ለኢትዮጵያ ከፍታ መትጋት እንዳለበት ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩ፣ የሕዝብ አገልጋዩ በሙያው፣ ወጣቱ በፈጠራው፣ ምሁሩ በዕውቀቱ፣ የሃይማኖት አባቶችና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትም ለሰላምና ለብሔራዊ መግባባት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም