ሰንደቅ ዓላማችን የሉዓላዊነታችን፣ የአብሮነታችንና የአንድነታችን መገለጫ በመሆኑ የተለየ ክብር ይሰጠዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሰንደቅ ዓላማችን የሉዓላዊነታችን፣ የአብሮነታችንና የአንድነታችን መገለጫ በመሆኑ የተለየ ክብር ይሰጠዋል
ጅግጅጋ፣ ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ)፦ ሰንደቅ ዓላማችን የሉዓላዊነታችን፣ የአብሮነታችንና የአንድነታችን መገለጫ በመሆኑ የተለየ ክብር ይሰጠዋል ሲሉ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ሙበሽር ዱበድ ገለጹ።
19ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሐሳብ በጅግጅጋ ከተማ ተከብሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ሙበሽር ዱበድ እንዳሉት፤ ሰንደቅ ዓላማችን የሉዓላዊነታችን፣ የአብሮነታችንና የአንድነታችን መገለጫ በመሆኑ የተለየ ክብር ይሰጠዋል።
ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያሏት ሀገር መሆኗን ተናግረው፤ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር ለአንድነታችን መጠናከር ድርሻው የማይተካ መሆኑን ገልጸዋል።
አፈ ጉባኤው ሰንደቅ ዓላማ የአንድነት መሠረትና አርማ መሆኑን አንስተው፣ ይህንን የበለጠ መጠበቅ ይኖርብናል ብለዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር በአንድነትና በኅብረት የሚያስተሳስረን የጋራ ሀገርና ሰንደቅ ዓላማ እንዳለን በማስታወስ አንድነታችንን ማጠናከር ይኖርብናል።
በክልሉ የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት በማጠናከር የተመዘገቡ የልማት ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሠራ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
ከለውጡ በኋላ በሀገሪቱ በተገኘው አካታች የፖለቲካ ሥርዓት የክልሉ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና በሁሉም መስክ በንቃት ለመሳተፍ መልካም ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት አባላት፣ የክልሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ የክልሉ ፖሊስ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ተገኝተዋል።