ሠንደቅ ዓላማችን የሚያስተሳስረን የብሔራዊ መግባባት መገለጫ ምልክታችን ነው - ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ሠንደቅ ዓላማችን የሚያስተሳስረን የብሔራዊ መግባባት መገለጫ ምልክታችን ነው - ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ)፦ሠንደቅ ዓላማችን የሚያስተሳስረን የአንድነታችንና የብሔራዊ መግባባት መገለጫ ምልክታችን ነው ሲሉ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት 19ኛውን የብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማ ቀን የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች በተገኙበት አክብሯል፡፡
የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር በሀገራችን የባህል፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ ልዩነት ቢኖርም ሠንደቅ ዓላማችን የሚያስተሳስረን የአንድነታችንና የብሔራዊ መግባባት መገለጫ ምልክታችን ነው፡፡
ቀኑን ስናከበር ትውልዶች ተቀባብለው እዚህ ያደረሱትን የኢትዮጵያ ነጻነትና ሉዓላዊነት ለማስቀጠል ተጨማሪ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በማስታወስ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም ጥንት አያቶቻችና አባቶቻችን በደምና በአጥነት ኢትዮጵያን አጽንተው ለዚህ ክብር ስላበቁ ክብር ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ታሪክን ለማክብር ብቻ ሳይሆን፤ ወደ ፊት የሚጠብቀንን ኃላፊነትና መስዕዋትነት ጭምር አውቀን በመዘጋጀት የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት የሚያስከብሩ ስራዎችን መስራት ስንችል ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት፣ ከድህነት የመውጣትና ብልጽግናዋን የማረጋገጥ እና በሁለንተናዊ መልኩ ነጻነቷን ያከበረችና ራሷን ያስከበረች ሀገር ለመፍጠር ቃልን በተግባር መፈጸም ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ምርታማ እንድትሆን፤ ከድህነት እንድትወጣና የተትረፈረፈ ምርት ያላትና ለሌሎችም የምትተርፍ እንድትሆን የሚያስችል ስራ በየተሰማራንበት በመስራት ሉዓላዊነቷን በማረጋገጥ ሠንደቋን ከፍ ለማድረግ በአንድነት ልንረባረብ ይገባል ብለዋል።