ቀጥታ፡

ሰንደቅ አላማችን የአንድነታችን ምሰሶና የወል ምልክታችን ነው - ርእሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) 

ሆሳዕና ፤ ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ)፦ ሰንደቅ አላማችን የአንድነታችን ምሰሶና የወል ምልክታችን ነው ሲሉ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

19ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ ዓላማችን ለሀገራዊ መግባባትና ለአንድነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ በሆሳዕና ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ሰንደቅ አላማችን የአንድነታችን ምሰሶና የወል ምልክታችን ነው፡፡

የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሲከበር ፈተናዎችን በዓላማ ፅናት በመሻገር የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ እውን ለማድረግ ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የአንድነት ምሰሶና የጋራ ምልክታችን የሆነው ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ለወል ትርክት ግንባታ መሰረት ሆነዉ ከሚያገለግሉ ምልክቶች መካከል አንዱ መሆኑን አስረድተዋል።

ቀደምት አባቶች የሀገርን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በከፈሉት ዋጋ የሀገራቸውን ብሄራዊ ክብር አስጠብቀዉ ከማቆየት ባለፈ ሰንደቅ ዓላማችን በዓለም  ከፍ ብሎ እንዲታይ ማድረጋቸውን  ክብርና ኩራት እንዲሰማን አድርጓል ብለዋል።

በዓሉ ሲከበር በትውልድ ቅብብሎሽ የታየውን የሀገር ወዳድነትና የሰንደቅ ዓላማ ፍቅር ለተተኪው ትውልድ  ማስተላለፍ   ከወቅቱ ትውልድ የሚጠበቅ ሀላፊነት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

የዘመኑ አርበኝነት ትኩረቱ የምግብ ሉዋላዊነትን ማረጋገጥ ፣ ሉአላዊነታችንና ነፃነታችን የተሟላ ብሄራዊ ክብራችን በአለም አደባባይ ከፍ ያለ እንዲሆን መትጋት ነው ብለዋል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ የጀመረችውን የእመርታ ጉዞ ወደ ከፍታ ማማ ለማሸጋገር ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ማጠናከርና ሀገራዊ መግባባትን ማፅናት እንደሚሻም አንስተዋል።

አስተሳሳሪ ትርክትን መገንባት ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ መጎልበትና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዋስትና ነዉ ሲሉም ተናግረዋል።


 

ለህብረ ብሄራዊ አንድነት መጠናከርና ለሀገራዊ መግባባት መጠናከር የክልሉ ህዝብ የሚጠበቅበትን ሀላፊነት መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በመርሐ ግብሩ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ነኢማ ሙኒር ፤ በብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ዴላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የክልል ፣ የዞን ፣ የልዩ ወረዳና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም