የሰንደቅ አላማ ቀን በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
የሰንደቅ አላማ ቀን በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተከበረ
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ)፦የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመራሮችና ሰራተኞች 19ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ መርሃ ግብሮች አክብረዋል።
ቀኑ የተከበረው “ሰንደቅ-ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን!” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዘንድሮ የሰንደቅ-ዓላማ ቀን እንደ ሀገር የተለያዩ ድሎችንና ስኬቶችን በማስመዝገብ የኢትዮጵያን ከፍታ በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ባለበት ወቅት የምናከብረው ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ሰንደቅ-ዓላማቸውን ከፊት በማስቀደም የትኛውንም ወራሪ ኃይል ሲመክቱና ሉዓላዊነታቸውን ሲያስከብሩ መቆየታቸውን አውስተዋል።
የአሁኑም ትውልድ የሀገሩን ብሔራዊ ደኅንትና ጥቅም ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ አዳዲስ ታሪኮች ለመጻፍ በከፍተኛ የሀገር ፍቅር መንፈስ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመራሮችና አባላትም ኢትዮጵያን ከፍ በሚያደርጉ፤ ብሔራዊ ደኅንትና ጥቅምን በሚያረጋግጡ የተለያዩ ስምሪቶች ግንባር ቀደም በመሆን መሰለፋቸውንም ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያን በተጨባጭ ከፍ የሚያደርጉ ድሎች ይመዘገባሉ ያሉት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሉ ለዚህም ዛሬም በሰንደቅ-ዓላማው ፊት ቃል-ኪዳናችንን እናድሳለን ሲሉ መግለጻቸውን የአገልግሎቱ መረጃ ያመለክታል።