ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የሀገሪቱን አኩሪ ታሪኮች፣ድሎች፣ ገድሎችና ማንነት የሚወክል ነው - ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሀገሪቱን አኩሪ ታሪኮች፣ ድሎች፣ገድሎችና ማንነት የሚወክል መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች በተገኙበት ዛሬ ተከብሯል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የአገሪቱን አኩሪ ታሪኮች፣ ድሎች፣ ገድሎችና ማንነት የሚወክል መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር በአግባቡ ሲያስጠብቁ፣ ሀገራቸውን ሲያሳድጉና ሲያበለጽጉ እንዲሁም ታሪካቸውን ሲያስቀጥሉ በሰንደቅ ዓላማቸው ላይ ያላቸው ኩራት ይበልጥ እንደሚያጎላው ተናግረዋል።

ሰንደቅ ዓላማን ከፍ አድርጎ ለማውለብለብ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አስተዋፅኦ እና አበርክቶ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ሚኒስትሩ አመልክተዋል።


 

የሀገርን ሉዓላዊነትና ባንዲራን ለማስከበር በየድንበሩ መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ ጀግኖችን ታሳቢ በማድረግ፣እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተሰማራበት የስራ መስክ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ጥሪ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም