ቀጥታ፡

የሀገር ክብርና ምልክት የሆነውን ሰንደቅ አላማ ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ይገባል

ባህርዳር፤ ጥቅምት 2/2019(ኢዜአ) ፡-የሀገር ምልክት የሆነውን ሰንደቅ አላማ በክብር ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማሰረከብ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው ሲሉ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ገለፁ።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በሰንደቅ ዓላማ በዓል አከባበር ላይ እንደገለጹት ሰንደቅ ዓላማችን የአንድነታችን፣ የሉዓላዊነታችን አርማና የማንነታችን መገለጫ ነው።


 

በየዓመቱ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን የምናከብረው የአባቶቻችንን አርበኝነትና የሀገርን ታሪክ በመዘከር፣ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ የራሱን አሻራ በማስቀመጥ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ህብረ ብሔራዊ አንድነት በመገንባት የአገራችንን ልማትና ዕድገት በማፋጠን፣ በሰንደቅ ዓላማችን ብዝሃነታችንንና አንድነታችንን በማጽናት ላይ የጀመርነውን ተግባር ዳር ለማድረስ መረባረብ ይገባል ብለዋል።

የሀገር  ሉዓላዊነት እናስከብር ስንል ሰላማችንን በማስጠበቅና በማፅናት ሁላችንም በየተሰማራንበት የሥራ መስክ የተጣለብንን ኃላፊነት ለመወጣት በመትጋት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሰንደቅ ዓላማችን የታሪካችንና የማንነታችን አሻራ ነው ብለዋል።


 

ቀደምት አባቶቻችን ሀገራችንን በአድዋ ተራራ ከጣሊያን ወራሪ ኃይል ጋር ተፋልመው አጥንታቸውን ከስክሰውና ደማቸውን አፍስሰው ነፃ ሀገር ያስረከቡን በሰንደቅ ዓላማው ስር በመሰባሰብ ነው ብለዋል።

ከአባቶቻችን የተረከብናትን ሀገር እኛም ወቅቱ የሚጠይቀውን ሁለንተናዊ ትግል በማድረግ ሰንደቅ ዓላማችንን ከነሙሉ ክብሩ በመጠበቅ  ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ይኖርብናል ብለዋል።

ሰላምን በመጠበቅና ችግርን በውይይት በመፍታት የኢትዮጵያን የማንሰራራትና የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በሰንደቅ ዓላማ በዓል አከባበሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የመንግሥት ሰራተኞችና የፖሊስ ሠራዊት አባላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም