ቀጥታ፡

ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ሉዓላዊነትና የነፃነት ምልክት ነው - አፈ ጉባዔ አብዱሰላም ዋሪዎ

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ)፡- ሰንደቅ ዓላማ ማንነት የሚከበርበት፣ ሉዓላዊነት ከፍ ብሎ የሚታይበት የአንድነትና የፍቅር ዓርማ ነው ሲሉ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ አብዱሰላም ዋሪዎ ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ህዝብ፤ ታላቅ ርዕይ!

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በጥቅምት ወር የመጀመርያ ሳምንት ሰኞ የሚከበረው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን፣ በሕገ-መንግሥቱና በወጣው አዋጅ መሠረት የሀገር ነፃነት፣ ሉዓላዊነትና የሕዝቦች አብሮነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ በጋራ ለማሰብና ለማክበር የተደነገገ ታሪካዊ ዕለት ነው። 


 

በዘመናት ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያውያን የሀገርን ዳር ድንበር፣ ክብርና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ደምና ላባቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩትን ይህንን ታላቅ የጋራ ምልክት በክብር በማሰብ አደራውን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ያለመ ነው።

በዚህ መሠረት ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ “ሠንደቅ ዓላማችን ለሀገራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው ክብረ-በዓል፣ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ልዩ ልዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ተቋማት ግቢ የሠንደቅ ዓላማ መስቀል ሥነ-ሥርዓት፣ የሕዝብ መዝሙር ዝማሬ፣ የፓናል ውይይቶችና የተቋማት የሥራ ቁርጠኝነት መግለጫዎችን ያካተቱ የተለያዩ ሁነቶች በድምቀት ተካሂደዋል። 

ሁነቱ የተቋማት ሠራተኞችና አመራሮች በሠንደቅ ዓላማው ጥላ ሥር በመሰባሰብ የሀገርን ሰላም፣ ልማትና ብሔራዊ መግባባት ለማጠናከር ያላቸውን ዝግጁነት ያደሱበት አጋጣሚ ነው።

በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ አቶ አብዱሰላም ዋሪዎ የሀገር አንድነት ምስጢር በጋራ ትግል ውስጥ ታንጾ በሰንደቅ ዓላማችን ወጥቶ የሚታይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በልጆቿ ውድ መስዋዕትነት ላይ የተገነባ መሆኑን አፈ ጉባዔው ገልጸው፤ ሰንደቅ ዓላማችንም የአባቶቻችን ተጋድሎና የከፈሉት መስዋዕትነት ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።


 

የበለጸገችና በኢኮኖሚ የጠነከረች ሀገር የምትገነባው ለሀገር ሲሉ ውድ ሕይወታቸውን በሰጡ ጀግኖች መሆኑን ያስታወሱት አፈ ጉባዔው፤ ይህንን ታሪካዊ በዓል ስናከብር ዳር እስከ ዳር ሀገራቸውን እያከበሩ ለሚገኙት ጀግኖቻችን ትልቅ ክብርና ፍቅር በመስጠት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

በሀገርም ሆነ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ልዩ ልዩ ፈተናዎችን አልፎ በነፃነት ምድር ላይ ሰንደቅ ዓላማን ከፍ አድርጎ ማወለብለብ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣው የሀገር ፍቅር፣ የጽናትና የጀግንነት ውጤት መሆኑንም ተናግረዋል።

የክልሉ ሕዝብና አመራር የመደመር መንግሥት የልማትና የብልፅግና ግቦችን ለማሳካት፣ እንዲሁም የሀገርን ሉዓላዊነት የሚጋፉ ጠላቶችን በመመከት የኢትዮጵያን ታላቅነትና የሰንደቅ ዓላማዋን ከፍታ ለማስቀጠል በሙሉ አንድነትና ቁርጠኝነት የተስማሙበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑንም ተናግረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም