መንግሥት ሰላምን ለማጽናትና ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር ሁልጊዜም ቁርጠኛ ነው - ፕሬዚደንት ታዬ አጽቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት ሰላምን ለማጽናትና ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር ሁልጊዜም ቁርጠኛ ነው - ፕሬዚደንት ታዬ አጽቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ)፦ መንግሥት ሰላምን ለማጽናትና ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር ሁልጊዜም ቁርጠኛ አቋም አለው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ፡፡
19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን "ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን" በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየተከበረ በሚገኘው በዓል ላይ ፕሬዚደንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሕመድ ሽዴ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ተገኝተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ፍቃዱ ተሰማ እና ሌሎች እንግዶችም በበዓሉ ላይ ታድመዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያውያን በብዝኃነት ውስጥ ያለውን ውበት አክብረን፣ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሃሳቦች ላይ ተመሥርተን ዘላቂ ሰላም፣ ጠንካራ ኢኮኖሚና ዘመናዊ ሥርዓተ መንግሥት መገንባት ይገባናል ብለዋል።
በመካከላችን ያሉ የሃሳብና የፖለቲካ ልዩነቶችን ከስሜታዊነትና ከግብታዊነት ወጥተን፣ በሰከነ መንገድ መደማመጥና መመካከርን በማስቀደም መፍታት እንደሚገባም አሳስበዋል።
መንግሥት ሰላምን ለማጽናትና ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር ሁልጊዜም ቁርጠኛ አቋም እንዳለው በመግለጽ፣ ግጭት የጥፋት ጎዳና፣ ሰላም ደግሞ የልባሞች መንገድ በመሆኑ የሰላምን መንገድ መከተል ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ዘመናዊ የፖለቲካ ፍኖት በአግባቡና ኢትዮጵያን በሚገልጽ መልኩ ማዘመንና አጥብቆ መያዝ ብልህነት እንደሆነም አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ላይ ጥፋት ለሚያስቡ፣ በአንደበታቸው ሞትንና ጥፋትን ለሚሰብኩና በጥፋት ምግባራቸው ለሚታበዩ ሁሉ መስመር የምናስይዝበት ወቅት ላይ ደርሰናል ብለዋል።
አመጽና ጥፋትን እንደ ትውልድ ዕዳ ለማሸጋገር ለሚታትሩትም ጊዜው የሥልጣኔ በመሆኑ ከዘመኑ ጋር አብረው እንዲራመዱ አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ሀገርን የማዘመን፣ የማበልጸግ፣ የማጽናትና ወደፊት የማራመድ እንጂ ወደኋላ የመመለስ ጉዞ ሊኖራት እንደማይገባ ገልጸዋል።
ፖለቲካዊ ሴራን ተንተርሶ ለክፋት የመጣመር ዘመንም እንዳለፈ ተናግረዋል።
በአንጻሩ የኢትዮጵያ መንገድ ቀጣይነትና በጎነት ያለው መሆኑን ጠቁመው፣ ዘመናችንን ሁሉ በዚሁ መንፈስ ለማጽናት የወሰነ ትውልድ መፍጠር እንደተቻለ አስረድተዋል።
ይህ እሳቤ በቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትና ትብብር ላይ የተመሠረተውን ፍትሐዊ የባሕር በር የማግኘትና የመጠቀም መብታችንን የሚያረጋግጥ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።
ይህም በሰላማዊ ዲፕሎማሲና በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚከናወን እንደሆነም አብራርተዋል።