የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የዘመኑ ወሳኝ አርበኝነት ነው - አፈ-ጉባዔ አሕመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የዘመኑ ወሳኝ አርበኝነት ነው - አፈ-ጉባዔ አሕመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የዘመኑ ወሳኝ አርበኝነት መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አሕመድ ሽዴ ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ
19ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሃሳብ በመከበር ላይ ይገኛል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሕመድ ሽዴ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በተገኙበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየተከበረ በሚገኘው በዓል ላይ ተገኝተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሕመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሰንደቅ ዓላማችን የኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ የተጻፈበት የጽናትና የጀግንነታችን ምልክት እንዲሁም የነፃነትና የሉዓላዊነት መገለጫችን ነው።
የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 መሠረት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሪፐብሊኩ ሉዓላዊነትና የሕዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት መገለጫ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህ መሠረት ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር የሕብረ ብሔራዊ አንድነትና የሉዓላዊነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ኃላፊነት የታሪክ፣ የሕግና የሕዝብ አደራ በመሆኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በከፍተኛ ቁርጠኝነትና ትጋት እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ስለዚህ ሰንደቅ ዓላማን ማክበር፣ ሀገርን ማክበር፣ ለሀገር የተከፈለውን ዋጋ ማስታወስና ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ የጋራ ኃላፊነት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሀገራችን አያሌ የሥልጣኔ ሥሮች አሏት ያሉት አፈ-ጉባኤ አሕመድ፤ እነዚህ ብዙ ሥልጣኔዎች ለዘመናዊት ኢትዮጵያ የሚሆኑ እሴቶችን ማበርከታቸውን አብራርተዋል።
እነዚህ እሴቶች ተደምረውና ከነገዋ ኢትዮጵያ ጋር ተጣጥመው ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ ግንባታ በማዋል ማስቀጠል እንደሚገባ አንስተዋል።
በብዙ የኢትዮጵያ ሥልጣኔዎች ከተገኙ እሴቶች መካከል አንዱ አርበኝነት መሆኑንም አስረድተዋል።
አርበኝነት ለሀገርና ለወገን ሲሉ በራስ ተነሳሽነትና መስዋዕትነት መክፈልን የሚመለከት እሴት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ይህንን የሰንደቅ ዓላማ በዓል የምናከብረው በሁሉም ዘርፎች በራስ ተነሳሽነት ለሀገርና ለወገን ሲባል የሚከፈለውን መስዋዕትነት ከማሰብ ጋር መሆኑን ጠቅሰዋል።
ስለዚህም በሁሉም ዘርፍ ኢትዮጵያ ራሷን ችላ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷን እንድታስከብር ዛሬም በአርበኝነት መንፈስ መነሳት እንደሚገባ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለዘመናት በተለያዩ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ልማዶችና እምነቶች ውስጥ ቢኖሩም በጋራ ታሪክና በጋራ ሀገር የተሳሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የባህል፣ የቋንቋና ሌሎች ልዩነቶችን እንደ ሀብት ተቀብለን የጋራ እሴቶቻችንን አጠናክሮ መጓዝ የዘመናችን ትልቁ ተግባር መሆኑን አመላክተዋል።