የሠንደቅ ዓላማ ቀን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ያለውን ፍቅር፣ ክብርና ቃል ኪዳን የሚያድስበት ታላቅ ብሔራዊ ቀን ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የሠንደቅ ዓላማ ቀን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ያለውን ፍቅር፣ ክብርና ቃል ኪዳን የሚያድስበት ታላቅ ብሔራዊ ቀን ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ)፦ የሠንደቅ ዓላማ ቀን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ያለውን ፍቅር፣ ክብርና ቃል ኪዳን በልቡ የሚያድስበት ታላቅ ብሔራዊ ቀን ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ፡፡
19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን "ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ በመላ ሀገሪቱ እየተከበረ ይገኛል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየተከበረ በሚገኘው የሠንደቅ ዓላማ ቀን ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሕመድ ሽዴ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ተገኝተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ፍቃዱ ተሰማ እና ሌሎች እንግዶችም ታድመዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፣ "ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን" በሚል መሪ ሃሳብ ለሚከበረው 19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ የሠንደቅ ዓላማ ቀን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ያለውን ፍቅር፣ ክብርና ቃል ኪዳን በልቡ የሚያድስበት ታላቅ ብሔራዊ ቀን መሆኑን ገልጸዋል።
በዕለቱ ብሔራዊ አንድነትን በጋራ የምናጎለብትበትና የነገውን ብሩህ ተስፋችንን የምናጠናክርበት ነው ብለዋል።
ሠንደቅ ዓላማ የብሔራዊ ኅብረትና የአንድነታችን ማሳያ፣ የዜጎች ሀገራዊ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት መገለጫ፣ እንዲሁም ታሪካዊና ማኅበራዊ ትስስራችንና የሥነ ልቦና አንድነታችን ማጽኛ ምልክት መሆኑን አመልክተዋል።
ሠንደቅ ዓላማ የመስዋዕትነት፣ የነጻነት፣ የልዕልና እና የግዛት አንድነታችን ምልክት እንዲሁም የሕዝቦች እኩልነትና ኅብረት ሕያው ምስክር መሆኑንም ተናግረዋል።
ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ደማቸውንና አጥንታቸውን ገብረው ውድ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ባስከበሩት ክብር፣ ሠንደቅ ዓላማችን በልባችን ታትሞ የቆየ የአሸናፊነትና የነጻነት ሰንደቅ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዓመታት ነጻነቷንና ልዕልናዋን አስጠብቃ ታፍራና ተከብራ የኖረች ታላቅ ሀገር መሆኗንም አውስተዋል።
ይህ ሁሉ ውበትና ኅብረ ብሔራዊ ጥንካሬ የሚገለጠው በብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማችን ነው ብለዋል።
ብዙ ፈተናዎች ውስጥ እያለፍን እንኳን ታላላቅ ፕሮጀክቶችን አጠናቀናል፣ በምግብ ራስን መቻል ላይ ርምጃ አድርገናል፣ የመከላከያና የደኅንነት ዘርፎችን ይበልጥ አዘምነናል፣ በማኅበራዊ ዘርፎችም ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበናል ብለዋል።
የቀጣዩ የዕድገት ጉዟችን ዋና ዓላማ ኢኮኖሚያዊ ልዕልናችንን ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥና ሀገራችንን ከማንኛውም ዓይነት ጥገኝነት ነጻ ማውጣት መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ፣ እንዲሁም የተፈጥሮ ጋዝ ሀብትን ለኃይልና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የመጠቀም ጥረት የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጎተራቸው ሞልቶ እንዲትረፈረፍ አቅም የሚፈጥሩ ብሔራዊ ፕሮጀክቶች እንደሆኑ አስረድተዋል።
እንዲህ ያሉ ታላላቅ ሃሳቦችና ፕሮጀክቶች ውጤታማ የሚሆኑት ብሔራዊ አንድነታችን ሲጠናከርና ሰላማችን አስተማማኝ ሲሆን መሆኑን አመልክተዋል።