የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ተሳትፎ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ተሳትፎ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2 /2018 (ኢዜአ)፦ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 17ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።
በማጣሪያው ላይ ዘጠኝ ሀገራት በሶስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ማድረግ ጀምረዋል።
በምድብ ሁለት የምትገኘው ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ዛሬ ከብሩንዲ ጋር ከቀኑ 11 ሰዓት በኪጋሊ ጨዋታውን ያደርጋል።
በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለማጣሪያ በሀገር ቤት ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቶ መስከረም 26 2019 ዓ.ም ኪጋሊ መድረሱ ይታወቃል።
ቡድኑ ባለፉት ቀናት ለመጀመሪያ ጨዋታ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የተመለመሉት በብሔራዊ ካምፒንግ ምልመላ እና ከታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ ነው።
የተጋጣሚው የብሩንዲ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሀገሬው ዜጋ ሴድሪክ ካሴ የሚመራ ነው።
ብሔራዊ ቡድኑ ለማጣሪያ ውድድሩ ለአንድ ወር ገደማ በቡጁምቡራ ዝግጅቱን በማድረግ ወደ ኪጋሊ አቅንቷል።
ብሩንዲ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ በዩጋንዳ የ 8 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል።
ጨዋታው ኢትዮጵያ በድል ማጣሪያውን ለመጀመር፣ ብሩንዲ በውድድሩ ለመቆየት የሚያደርጉት ነው።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ የምድብ ጨዋታውን ጥቅምት 4 ከዩጋንዳ ጋር ያደርጋል።
ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ከምድቡ አንደኛ መውጣት ወይም ከሶስቱ ምድቦች ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል።
በምድብ አንድ አዘጋጇ ሩዋንዳ ከሱዳን ከቀኑ ሰባት ላይ ጨዋታዋን ታደርጋለች።
የማጣሪያ ውድድሩ እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2019 ዓ.ም ይቆያል።
በውድድሩ ከአንድ እስከ ሶስት የሚወጡ ሀገራት ሴካፋ ዞንን ወክለው በአፍሪካ ዋንጫ ይሳተፋሉ።
17ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ በ2027 በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።