ኮቨንተሪ ሲቲ ከኒውካስትል ዩናይትድ ፤ የሊጉ የስድስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
ኮቨንተሪ ሲቲ ከኒውካስትል ዩናይትድ ፤ የሊጉ የስድስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2 /2019 (ኢዜአ):- የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል።
ምሽት አራት ሰዓት ላይ ኮቨንተሪ ሲቲ ከኒውካስትል ዩናይትድ በኮቨንተሪ ቢውልዲንግ ሶሳይቲ አሬና ይጫወታሉ።
አዲስ አዳጊው ኮቨንተሪ ሲቲ በሶስት ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ኮቨንተሪ ከአራት ተከታታይ የሊግ ሽንፈቶች በኋላ በአምስተኛ ሳምንት ኖቲንግሃም ፎረስትን 1 ለ 0 በማሸነፍ የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል።
ተጋጣሚው ኒውካስትል ዩናይትድ በስምንት ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ በአምስተኛ ሳምንት አዲስ አዳጊውን ሁል ሲቲን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ሁለቱ ክለቦች በሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ13ኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 12 ጨዋታዎች ኒውካስትል ዩናይትድን ስምንቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ኮቨንተሪ ሲቲ በሁለቱ ድል ሲቀናው በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
በ12ቱ ጨዋታዎች ላይ ኒውካስትል 24 ጎሎችን ሲያስቆጥር ኮቨንተሪ በበኩሉ 13 ግቦችን ከመረብ ጋር አገናኝቷል።
ሁለቱ ክለቦች ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ የተገናኙት እ.አ.አ በ2001 ዓመት ነው። በወቅቱ ኒውካስትል ዩናይትድ 3 ለ 1 ማሸነፉ አይዘነጋም።
ቡድኖቹ ከ25 ዓመታት በኋላ ዳግም በሊጉ ይገናኛሉ።
ኮቨንተሪ ሲቲ ከ25 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መመለሱ ይታወቃል።
ሁለቱ ክለቦች በአሸናፊነት ጉዟቸው ለመቀጠል የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የ36 ዓመቱ ጆን ብሩክስ ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት እንዲመሩ ተመድበዋል።