ቀጥታ፡

ሰንደቅ አላማ የሀገር ህብረ ብሔራዊ አንድነት እና የሉዓላዊነት መገለጫ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2019 (ኢዜአ)፦ ሰንደቅ አላማ የሀገር ህብረ ብሔራዊ አንድነት እና የሉዓላዊነት መገለጫ ነው ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አህመድ ሽዴ ገለጹ።

19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተገኙበት በመከበር ላይ ይገኛል።

“ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” ቀኑ የሚከበርበት መሪ ሐሳብ ነው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አህመድ ሽዴ ለሰንደቅ አላማ ቀን እንኳን አደረሳችሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል።

ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው ይህ ቀን ወሳኝ እና ወቅታዊነቱ በጠበቀ መሪ ሀሳብ እየተከበረ መሆኑን አመልክተዋል።

ሰንደቅ አላማችን የኢትዮጵያ የጋራ ታሪክ የተጻፈበት፣ የጽናትና ጀግንነታችን ምልክት እንዲሁም የነጻነት እና የሉዓላዊነት መገለጫችን ነው ብለዋል።

ምክር ቤቱ በህግ በተሰጠው ስልጣና ሃላፊነት ይህንን ብሔራዊ በዓል በበላይነት የማስተባበር፣ የመምራት እና የሰንደቅ አላማን ክብር ከፍ የሚያደርጉ ስራዎችን እንደሚያከናውን አንስተዋል።

ምክር ቤቱ ይህን የታሪክ እና የህዝብ አደራ ተቀብሎ ይህ ታላቅ ሁነት በማሰናዳቱ ከፍተኛ ኩራት ይሰማል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም