የትግራይ ክልልን የሰላም እና የልማት ማዕከልነት የማረጋገጥ ጉዞ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ክልልን የሰላም እና የልማት ማዕከልነት የማረጋገጥ ጉዞ
ከትራንስፖርት አገልግሎት እስከ ሰብዓዊ ድጋፍ፦ የትግራይ ክልልን የሰላም እና የልማት ማዕከልነት የማረጋገጥ ጉዞ
የሕወሓት ቡድን አጥፊ አካሄድ የትግራይ ክልልን ሕዝብ ሰላም፣ ደህንነትና የወደፊት ተስፋ አደጋ ላይ የሚጥል ነው። ቡድኑ ከሕዝብ ሰላማዊ ሕይወት ይልቅ የራሱን ቡድናዊ ጥቅም በማስቀደሙ ምክንያት፣ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዳይረጋገጥና ሕዝቡም ወደ መደበኛ ሕይወቱ እንዳይመለስ ትልቅ እንቅፋት ሲሆን ቆይቷል። በተለይም ወጣቶችን በግዳጅ ወደ ጦርነት መውሰዱ፣ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው ማራቁና የሚፈጽማቸው ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት በሕዝብ ላይ የሚያደርሳቸው ከባድ በደሎች ናቸው።
የትግራይ ክልል ሕዝብ ከማንኛውም ጊዜ በላይ የሰላምን አስፈላጊነት በጽኑ ይረዳል። የወጣቶችም ፍላጎት በጦርነት ማለቅ ሳይሆን በትምህርት፣ በሥራና በልማት የተሞላ ተስፋ ያለው የወደፊት ዕድል ማግኘት ነው። የማንኛውም ቡድን ጥቅም ከሕዝብ ሕይወትና ከዜጎች መጻኢ ዕድል በላይ ሊበልጥ አይችልምና።
የፌዴራል መንግሥት የትግራይ ክልል ልክ እንደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሰላም፣ የልማትና የዕድገት ማዕከል እንዲሆን የሚያደርገው ጥረት በተግባራዊ እርምጃዎች የታጀበ ነው። ለዚህም ለሰላም በሩን ክፍት በማድረግ፣ በትዕግሥትና በሆደ ሰፊነት መንቀሳቀስ እንዲሁም ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ በመሆን ለዘላቂ ሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር አረጋግጧል።
ታጣቂዎች ወደ ተሃድሶ ገብተው ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ የቅበላ ማዕከላትን ማዘጋጀቱ በአብነት የሚጠቀስ ነው። በትግራይ ክልል በተለያዩ ዞኖችና ከተሞች የተዘጋጁት የተሃድሶ ቅበላ ማዕከላት ታጣቂዎች ከጦርነት ወጥተው ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲሸጋገሩ ዕድል ፈጥሯል፣ አሁንም እየፈጠረ ይገኛል። ይህም የግጭት አዙሪትን ለመስበር፣ የሰው ሕይወትን ለመታደግና ለልማት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ ነው።
በተመሳሳይ በአላማጣ ከተማ ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች በፌዴራል መንግሥት ወጪ የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ መጀመሩ የሕዝቡን አስቸኳይ ፍላጎት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት ያሳያል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ድጋፉን ማድረስ መቻሉ ዜጎች በችግር ውስጥ ሲሆኑ ፈጥኖ የመድረስና የሰብዓዊ ኃላፊነትን የመወጣት አስፈላጊነት በእጅጉ ያጎላል።
በሕወሓት ህገ ወጥ ተግባር በረራው ተቋርጦ የነበረው ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ የአውሮፕላን በረራ እንደገና መጀመሩ ሌላው ተጨባጭ እርምጃ ነው። የትራንስፖርት ግንኙነት መመለስ የሰዎችን እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ፣ የንግድና የሥራ ግንኙነቶችን ለማጠናከር፣ ለቤተሰብና ማህበራዊ ግንኙነትን መልሶ ለመገንባት እንዲሁም የክልሉን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ጠቃሚ ነው።
የተቋረጡ አገልግሎቶች መመለስ ለሰላም ግንባታና ለልማት የሚያስፈልገውን መሠረትም በእጅጉ ያጠናክራል።
በአጠቃላይ በትግራይ የተሃድሶ ማዕከላት መዘጋጀት፣ ለተጎጂ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ መድረስና የአየር በረራ ዳግም መጀመር የሚያሳዩት አንድ ወሳኝ መልዕክት አለ፤ ሰላም በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ይገነባል። ይህ የክልሉ ሕዝብ ወደ መደበኛ ሕይወት እንዲመለስ፣ ልጆቹ በሰላም እንዲማሩ፣ ወጣቶቹ በሥራና በልማት እንዲሳተፉ እና ክልሉ ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ጋር በእኩልነት እንዲያድግ በመንግሥት በኩል የሚደረገውን ያላሰለሰ ጥረት የሚያረጋግጡ ናቸው።
የሰላምን ዕድል መጠቀም የሕዝብን ሕይወት ከመታደግ ባለፈ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ህልውና፣ አንድነትና የጋራ የወደፊት ተስፋ ለማጠናከር ወሳኝ ነው።