ሰንደቅ ዓላማችን የማንነታችን ማኅተም በመሆኑ ልዩ ክብር ልንሰጠው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሰንደቅ ዓላማችን የማንነታችን ማኅተም በመሆኑ ልዩ ክብር ልንሰጠው ይገባል
ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 1 /2019 (ኢዜአ):- ሰንደቅ ዓላማችን የክብራችንና የማንነታችን ማህተም ብቻም ሳይሆን ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የሚያጠናክር በመሆኑ ልዩ ክብር ልንሰጠው ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ይስሃቅ አብርሃም ተናገሩ።
‹‹ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን›› በሚል መሪ ሐሳብ 19ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀንን አስመልክቶ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።
የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በፓናል ውይይቱ ላይ እንዳሉት፤ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማችን የክብራችንና የማንነታችን ማኅተም በመሆኑ ልዩ ክብር ልንሰጠው ይገባል።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ህብረ ብሔራዊ አንድነትንና ዘላቂ መግባባትን የሚያጠናክር የጋራ ዓርማ መሆኑንም አመልክተዋል።
ዕለቱ ቀደምት አባቶች ለሰንደቅ ዓላማው ክብርና ለሀገራቸው ሉዓላዊነት ሲሉ የከፈሉትን መስዋዕትነት የምንዘክርበት ጭምር ነው ሲሉ አፈ ጉባኤው ተናግረዋል።
በዓሉ በየዓመቱ መከበሩ ዜጎች ስለ ሰንደቅ ዓላማ ክብርና ትርጓሜ በተገቢው መንገድ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም አብራርተዋል።
አክለውም የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር አንድነቷ የተጠበቀና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ቃላችንን የምናድስበት ዕለት ጭምር ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሰንደቅ ዓላማችን ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባትና የሕዝቦችን አንድነትና አብሮነት ለማጠናከር የሚያስችል ዓርማ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሰንደቅ ዓላማው ኢትዮጵያዊ አንድነታችን የሚጠናከርበትና ማንነታችን በዓለም መድረክ ጎልቶ እንዲተዋወቅ የሚያደርግ ነውም ብለዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ ስለ ሰንደቅ ዓላማ ትርጓሜ የሚያስረዳ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
19ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን›› በሚል መሪ ሐሳብ ነገ ሰኞ፣ ጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም. በሀገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት ይከበራል።