የክልሉ መንግስት የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት እንዲጠናቀቁ ርብርብ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ መንግስት የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት እንዲጠናቀቁ ርብርብ ያደርጋል
ወላይታ ሶዶ ፤ ጥቅምት 1 /2019 (ኢዜአ):- የክልሉ መንግስት የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት እንዲጠናቀቁ ርብርብ እንደሚያደርግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) ተናገሩ።
የክልሉ ምክር ቤት አባላትና ከፍተኛ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች በወላይታ ሶዶ ከተማ በግንባታ ላይ የሚገኙ የተለያዩ ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ሂደትን ተመልክተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ መጠናቀቅ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ለአካባቢው እንቅስቃሴ መነቃቃት ያለው ድርሻ የጎላ ነው።
የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ትኩረት ከተሰጣቸው ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን ጠቁመው፣ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቅ የሰው ኃይል፣ የሥራ ሰዓትና የማሽነሪዎችን ቁጥር በመጨመር ሌት ተቀን መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል የወላይታ ሶዶ ከተማ የኮንክሪትና የአስፋልት መንገድ ግንባታ መጓተት ከተማዋን ለንግድም ሆነ ለሕዝብ እንቅስቃሴ እንቅፋት መፍጠሩ በሕዝቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ማስነሳቱን አንስተዋል።
በመሆኑም በመንገዱ ሥራ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት ሥራው በፍጥነትና በጥራት እንዲጠናቀቅ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
በከተማዋ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራ የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለኢንቨስትመንት ደግሞ ተመራጭ የሚያደርጋት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የግንባታ ሥራው በጥራትና በፍጥነት እንዲከናወን የተለየ የክትትል ሥርዓት በመዘርጋት እንዲመራ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነባር ሕንፃ ላይ የእሳት አደጋ በመድረሱ የጤና አገልግሎት ሥርዓቱን ማስተጓጎሉ ሕዝቡ ዘንድ ቅሬታ አስነስቶ መቆየቱን አንስተዋል።
ችግሩን ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ የተጀመረውን ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ የጤና አገልግሎት ሥርዓቱን ለማሻሻል በቁርጠኝነት እንዲሠራ አሳስበዋል።
የክልሉ መንግሥትም እነዚህ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የወላይታ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ ፋንታ በበኩላቸው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሕንፃ ጥገናና ዕድሳት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት ይሠራል ብለዋል።
የወላይታ ሶዶ አውሮፕላን ማረፊያ ሥራን በተቀመጠለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጭ ጭምር እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአንዋር ሰይድ አጠቃላይ ሥራ ተቋራጭ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አንዋር ሰይድ ናቸው።