በመዲናዋ የሥራ አፈፃፀም በህብረተሰቡ ዘንድ በተገኙ ተጨባጭ ውጤቶችና ጥቅሞች ላይ ተመስርቶ እንዲመዘን ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የሥራ አፈፃፀም በህብረተሰቡ ዘንድ በተገኙ ተጨባጭ ውጤቶችና ጥቅሞች ላይ ተመስርቶ እንዲመዘን ይደረጋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1 /2019 (ኢዜአ):- በአዲስ አበባ ከተማ የሥራ አፈጻጸም በህብረተሰቡ ዘንድ በተገኙ ተጨባጭ ውጤቶችና ጥቅሞች ላይ ተመስርቶ እንዲመዘን ይደረጋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲያካሒድ የቆየውን የ2019 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሞ የቀጣይ ሶስት ወራት የትኩረት አቅጣጫ በማስቀመጥ አጠናቋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የከተማዋ ነዋሪዎች የሰጡንን ኃላፊነት በታማኝነትና በብቃት ተወጥተናል ብለዋል፡፡
በነዋሪዎች የኑሮ ሁኔታና ተጠቃሚነት ላይ አዎንታዊ ለውጥ ያመጡ እና ለቀጣይ ሥራዎች መሠረት የጣሉ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከታቀደው በላይ በመፈጸም አበረታችና ምሳሌ የሚሆኑ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ 2 ሺህ 500 ያህል አዳዲስ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ ከ4 ሺህ 200 በላይ ቤቶች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን አብራርተዋል።
ማህበራዊ ደግነትን እና ርህራሄን በማጎልበት በኩልም የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት በስኬት መከናወኑን ተናግረዋል።
በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ማከናወንን ጨምሮ ሳይጠናቀቁ የነበሩ በርካታ ግንባታዎች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ መደረጉን ጠቅሰዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተሰራው ሥራ በፈረቃ ይሰጡ የነበሩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ወደ ተቀመጠው ስታንዳርድ እንዲመጡ መደረጉን አንስተዋል፡፡
አዳዲስ የጤናና የትምህርት ተቋማት ተገንብተው ወደ ሥራ መግባታቸውን እንዲሁም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን አመልክተዋል፡፡
በከተማዋ የሥራ አፈጻጸምን በቁጥርና በመቶኛ ብቻ ከማስቀመጥ ባለፈ ለህብረተሰቡ የተገኘውን ትክክለኛ ውጤት እና ጥቅም መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲመዘን ይደረጋል ብለዋል፡፡
ሪፖርቶችን በዲጂታል መንገድ በመደገፍ ተግባራዊ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡
ይህ አቅጣጫ ከተማዋ ያስመዘገበችውን ስኬት አስቀጥሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከናወኑ ሰፊ የሥራ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና ፕላን ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፤ የሚዘጋጁ ሪፖርቶች ይበልጥ እውነተኛ፣ ጥራት ያላቸውና በማስረጃ የሚደገፉ እንዲሆኑ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
በሁሉም ተቋማት የሚቀርቡ ሪፖርቶች አንድ ዓይነትና ወጥነት ያለው ፎርማት እንዲኖረው እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር) ፤ ሩብ ዓመቱ ከከተማ እስከ ወረዳ ያለው አመራር በሙሉ ትኩረትና አቅም ስራዎችን ያከናወነበት ህብረተሰቡም በንቃት የተሳተፈበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ከመላው የኢትዮጵያ ክፍል የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በከተማዋ ተገኝተው በሀገራዊ የቀጣይ ዕጣ ፈንታ ዙሪያ የመከሩበትና ውጤት የተመዘገበበት እንደነበር አውስተዋል፡፡