በአማራ ክልል በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የልማት ሥራ ተሰርቷል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የልማት ሥራ ተሰርቷል
ደብረ ብርሃን/ ባህር ዳር ፤ ጥቅምት 1 /2019 (ኢዜአ):-በአማራ ክልል በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አቅመ ደካሞችንና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረገ ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የልማት ሥራ መሠራቱን የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያና የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ አካሄዷል።
የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ እንደገለፁት፤ በክልሉ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የልማት ሥራ ተሰርቷል።
በክልሉ በክረምቱ ወቅት ከ10 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ የልማት ሥራዎችን ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።
በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርናና በሌሎች ዘርፎች አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፣ የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር የዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የጤና የበጎ ፈቃድ ሕክምና አገልግሎት አስተባባሪ ዶክተር ሐብታሙ መንጌ በበኩላቸው፣ አገልግሎቱ ለዜጎች የጤና ግልጋሎትን በሰፊው ተደራሽ ለማድረግ እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ከፍለው መታከም ለማይችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የምርመራና የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ማገዙን አስረድተዋል።
ይህም በየደረጃው ጤናማና አምራች ሕብረተሰብን በመፍጠር እየተመዘገበ ለሚገኘው ሀገራዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ በበኩላቸው፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሕክምና ተደራሽነትን እያረጋገጠ መሆኑን ገልጸው በክረምቱ የተካሄደውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋም በማስቀጠል ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በክረምትና በበጋ ወራት እየተካሄዱ የሚገኙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን አጠናክሮ በማስቀጠል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ናቸው።
በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው ተመሳሳይ መድረክ ላይ የተገኙት የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳለማው በበኩላቸው በጎ ፈቃደኞች በመሠረተ ልማት ጥገና፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እያከናወኑት ያለው ተግባር እንዲቀጥል ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሰብለ ዘውዱ በበኩላቸው፣ በከተማዋ በክረምቱ ከ239 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ከ251 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በጎ ፈቃደኞቹ ከ661 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የልማት ሥራ በነፃ ማበርከታቸውን ጠቁመው፣ በበጋው ወቅትም የበጎ ፈቃድ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።