ቀጥታ፡

ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ የአውሮፕላን በረራ አገልግሎት እንደገና በመጀመሩ በጣም ተደስተናል 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2019 (ኢዜአ)፦ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ የአውሮፕላን በረራ አገልግሎት እንደገና በመጀመሩ በጣም ተደስተናል ሲሉ ተጠቃሚዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀደም ሲል ጥቅምት 1 ቀን 2019 ዓ.ም ወደ መቀሌ ከተማ በረራ እንደሚጀምር ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ዛሬ በይፋ ጀምሯል።

በዚህም መሠረት ከአዲስ አበባ የተነሳው የአየር መንገዱ አውሮፕላን ዛሬ ማለዳ በመቀሌ ከተማ አሉላ አባ ነጋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አርፏል።

የአገልግሎቱን መጀመር ተከትሎም በርካታ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች በአውሮፕላን ማረፊያው በመገኘት የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እና ሌሎችም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ዜጎች የትራንስፖርት አገልግሎት እንደገና በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና ልማትን ለማፋጠን ያለውን ቁርጠኛ አቋምና ተግባራዊ እርምጃዎችን በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ መጀመሩ በክልሉ የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚያፋጥን ተናግረዋል።

አቶ አሸናፊ ጸጋዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ለሥራ ጉዳይ ወደ መቀሌ በሄዱበት ወቅት በረራው በመቋረጡ ምክንያት ለችግር ተዳርገው ቢቆዩም አሁን አገልግሎቱ በመጀመሩ ትልቅ ደስታ ተሰምቷቸዋል።

የአየር መንገዱ የበረራ አገልግሎት መጀመር የትግራይ ሕዝብ ከነበረበት ሁለገብ ችግር እንዲወጣ ከሚያግዙ አስፈላጊ እርምጃዎች አንዱ መሆኑንም ገልጸዋል።

ክልሉ ለተለያዩ መሠረታዊ ቁሳቁሶች እጥረት ተጋልጦ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ አሸናፊ፤ የፌደራል መንግሥት አሁን የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንደሚያጸና እምነታቸውን ገልጸዋል።

አቶ ናትኤል ሰለሞን በበኩላቸው፤ የበረራ አገልግሎቱ ዳግም በመጀመሩ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አክሎም የትግራይ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ሕዝብ መሆኑን በመግለጽ፤ የተጀመረው አበረታች የበረራ አገልግሎት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነት እንዳለው ተናግረዋል።

አቶ ሃድራት ኮት፤ የበረራ አገልግሎቱ ዳግም በመጀመሩ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸው፤ ይህም ለክልሉ ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም