የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን ለኢኮኖሚ ዕድገት ፋይዳው የጎላ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን ለኢኮኖሚ ዕድገት ፋይዳው የጎላ ነው
ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 1 /2019 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን ለቀጣናዊ ሰላምና ኢኮኖሚ ዕድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።
ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት ምስረታ ዳግም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲሰየሙ ኢትዮጵያን በሰጥቶ መቀበል መርህ የባሕር በር ባለቤት ለማድረግ እንደሚሠሩ መግለጻቸው ይታወሳል።
የባሕር በር ጥያቄው የማንንም ሀገር ሉዓላዊነትና ግዛት የሚጋፋ ሳይሆን፣ በሁለትዮሽ ውይይትና በፍትሐዊ የጋራ ጥቅም መርህ የሚፈጸም መሆን አለበት ማለታቸውም እንዲሁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን ለሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም፣ ዘላቂ ልማት እና የጋራ ብልፅግና መሠረት የሚጥል እንጂ የማንም ሀገር ስጋት እንዳልሆነ አብራርተዋል።
ይህን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን እንደገለፁትም፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን ለቀጣናዊ ሰላምና ኢኮኖሚ ዕድገት ፋይዳው የጎላ ነው።
በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁር ሰብለወንጌል ዋሲሁን (ዶ/ር) እንዳሉት፣ የባሕር በር ኢትዮጵያ ለጀመረችው የኢኮኖሚ ዕድገትና ዓለም አቀፋዊ የወጪና ገቢ ምርቶች የንግድ ሚዛንን ለማስጠበቅ መሠረት መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ተጀመሩ የዲፕሎማሲ ስራዎች ተገቢና ተቀባይነት ያላቸው ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
የባሕር በር ባለቤትን ጉዳይ የሉዓላዊነትና የህልውና ጉዳይ በመሆኑ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ያለ ምንም የፖለቲካ ልዩነት በጋራ ሊቆም ይገባል ብለዋል።
በጋምቤላ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ ያሲን በላይ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆኗ ለእሷ ብቻ ሳይሆን ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላም ያላትን ሚና ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የነበራትን የባሕር በር ያጣችው በተወሰኑ ቡድኖች የፖለቲካ ሴራ መሆኑን የገለጹት ምሁሩ፤ ይልቁንም ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር በቅርብ ርቀት ላይ እያለች፣ በርቀት ላይ የሚገኙ ብዙ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ሀገራት የባሕር በር የማግኘት ዓለም አቀፋዊ መብት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
በመሆኑም በሰጥቶ መቀበል ዲፕሎማሲያዊ ሂደት የተጀመረው የባሕር በር ጥያቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።