የሸማ ጥበብ-የጋሞዎች ባህላዊ ማንነት እና የኢኮኖሚ መሠረት - ኢዜአ አማርኛ
የሸማ ጥበብ-የጋሞዎች ባህላዊ ማንነት እና የኢኮኖሚ መሠረት
አርባ ምንጭ፤ ጥቅምት 1 /2019 (ኢዜአ):- የሸማ ጥበብ-- የጋሞዎች ባህላዊ ማንነት እና የኢኮኖሚ መሠረት
በሳሙኤል አየነው (ኢዜአ አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ)
በኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ጥበባት ታሪክ ውስጥ የጋሞ ማኅበረሰብ የሸማ ሥራ ልዩና የጎላ ስፍራ አለው። ከጥንት ጀምሮ ከጥጥ ምርት ጋር የተሳሰረው ይህ ዕውቀት፣ ልብስን ከመልበስ ፍላጎት አልፎ የትውልድ ማንነት፣ የውበት መግለጫ እና የታሪክ ማኅደር ሆኖ ዘልቋል። በጥጥ ፈትል ላይ በሚያርፉ ደማቅ ቀለማትና ልዩ ንድፎች የሚታወቀው የጋሞ የሸማ ጥበብ፣ እንደ «ዱንጉዛ» ያሉ የክብር አልባሳትን ለአለም በማስተዋወቅ አርባ ምንጭንና አካባቢዋን "የጥበብ ምድር" የሚያስብል እና የታሪክ ባለቤት አድርጓቸዋል።
የጋሞ የሸማ ጥበብ ተራ የሙያ ክህሎት ሳይሆን በቤተሰብ አባላት የጋራ ድርሻና ትብብር የሚከናወን፣ ትውልድ ከትውልድ የሚወርሰው ሕያው ባህላዊ እሴት ነው። ሴቶች ጥጥ በመፍተል፣ ወንዶች በዕውቀታቸው በመሸመን፣ ህፃናት ደግሞ በመደወር የሚካፈሉበት ይህ የሙያ ክፍፍል ማኅበራዊ ትስስርን ያጠናክራል።
ከባህላዊ መግለጫነቱ ባሻገር የጋሞዎች የሸማ ጥበብ ለአካባቢውና ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት የሀብት ምንጭ ነው። ሙሉ በሙሉ በእጅ በሚከናወነውና ሳይበረዝ በቆየው በዚህ ሀገር በቀል ጥበብ የተመረቱ አልባሳትና ብርድ ልብሶች፣ በአሁኑ ወቅት ከሀገር ውስጥ ገበያ አልፈው በዘመናዊ ዲዛይኖች በመታገዝ በአውሮፓና በአሜሪካ ገበያዎች ዘንድ ትልቅ አድናቆትን አትርፈዋል። ይህም ጥበቡ ለብዙዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዲኖረው አድርጎታል።
በሀገራችን ከሚታወቁ ሀገር በቀል ዕውቀቶች መካከል አንዱ የጋሞዎች መገለጫ የሆነው የሸማ ጥበብ ነው። የሸማ ጥበብ ደግሞ ከጥጥ ምርት የሚሠራ በመሆኑ ጋሞዎች ከጥጥ ምርት ጋር ያላቸው ቁርኝት ከጥንት ጀምሮ የዘለቀ ነው። ጥጥ ለጋሞዎች ከልብስ እስከ ጉርስ፣ ከጉርስ እስከ ውርስ በመሆን ትውልድ ተሻግሮ እያገለገለ የሚገኝ ሀብት ነው።
በተለያየ መልክ በመሠራቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ዜጎችን ቀልብ እያማለለ ያለው የሸማ ጥበብ "ጋሞ የጥበብ ምድር" ተብሎ እንዲጠራም ምክንያት ሆኗል። ይህን ተከትሎ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በ1890ዎቹ የጥበብ አልባሳት እንዲሠሩላቸው በሚል አፄ ምኒልክ በቁጥር 50 የሚሆኑ የሸማ ጥበብ ያላቸውን ጋሞዎች ከዶርዜ አካባቢ ወደ መሐል ሀገር እንደወሰዷቸው ይነገራል።
በዚህ መልክ የሸማ ጥበብና ዕውቀቱ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ መሐል ሀገር እና ሌሎች ትላልቅ ከተሞች የተስፋፋ ሲሆን፣ የአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካም ይህን ፀጋ ተከትሎ ሊመሠረት ችሏል።
በግብርና ልማት እና በሽመና የሚተዳደረው የጋሞ ማህበረሰብ በማሳው ጥጥን በስፋት ማምረት ከህልውናው ጋር የተያያዘ በመሆኑ ዛሬም ድረስ በአካባቢው ጥጥ በስፋት እየተመረተ ይገኛል።
የጋሞዎች የሸማ ጥበብ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ስፍራ ያለው፣ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረና ማንነትን የሚገልጽ ሀገር በቀል ዕውቀት ነው። በጥጥ ከሚሠሩ ባህላዊ አልባሳት መካከል አንዱ የማንነታቸው መገለጫ የሆነው ‹‹ዱንጉዛ›› ነው። ይህም የጋሞ ማህበረሰብ ታዋቂና የክብር ልብስ ሲሆን፣ ቀይ፣ ጥቁርና ቢጫ የመሳሰሉ ደማቅ ቀለሞችንና ልዩ ንድፎችን የያዘ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ እንደ ቁሌ፣ አሰራ፣ ፈርዣ፣ ቡሉኮ፣ ጋቢ፣ ኩታ፣ ባርኔጣ እና ያኖ የመሳሰሉ የተለያዩ የባህል ልብሶችና ብርድ ልብሶች ይመረታሉ። ልብሶቹ ውበትን ከማንጸባረቅ ባለፈ እንደ "ዮ ማስቃላ" ባሉ የዘመን መለወጫ በዓላት ከፍተኛ ቦታ አላቸው።
የሸማ ጥበብ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ፣ የቱሪዝም መሳቢያ እና የጋሞ ህዝብ የኢኮኖሚ መሠረት በመሆኑ ልጆች ከወላጆች የሚወርሱት ነገር ቢኖር አንዱ የሸማ ጥበብ ነው። የሸማ ሥራ የሚከናወነው እንደ ቤተሰብ የሥራ ድርሻ በመከፋፈል ሲሆን፣ በዚህም ሴቶች ጥጥ በመፍተል፣ ወንዶች በመሸመን እንዲሁም ልጆች በመደወር ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ።
የሸማ ጥበቡን ልዩ የሚያደርገው በእጅ ብቻ የሚሠራ፣ ያልተበረዘና ያልተከለሰ ሀገር በቀል ሀብት መሆኑ ነው። ይህም በአሁኑ ሰዓት በዘመናዊ ዲዛይን በመታገዝ ከሀገር ውስጥ እስከ አውሮፓና አሜሪካ ገበያዎች በስፋት የሚገኝ ሲሆን፣ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ የራሱን ድርሻ እያበረከተ ይገኛል።
በቅርቡ 6ኛው አለም አቀፍ የጥጥ ቀን ''ጥጥ ለበጎነት፡ በንግድ፣ እሴት በመጨመር እና በትብብር የበለጸገ ሕይወትን መገንባት'' በሚል መሪ ሐሳብ በታሽከንት፣ ኡዝቤኪስታን የተከበረ ሲሆን የጥጥ ምርትን ከጥሬ ዕቃነት ባሻገር እሴት በመጨመር ወደ ከፍተኛ ውጤት ማሸጋገርን፣ የዓለም አቀፍ ንግድ ዕድሎችን ማስፋፋትን እና የአምራች ማኅበረሰቦችን የኢኮኖሚ ተደራሽነት ማሳደግን ያለመ ውይይት በማካሄድ መጠናቀቁ ይታወሳል።