ሲዳማ ቡና የዋንጫ ክብሩን የማስጠበቅ ጉዞውን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚያደርገው ጨዋታ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
ሲዳማ ቡና የዋንጫ ክብሩን የማስጠበቅ ጉዞውን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚያደርገው ጨዋታ ይጀምራል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 1/2019 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል።
በዕለቱ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሲዳና ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሲዳማ ቡና በ2018 በ68 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉ ሻምፒዮን መሆኑ የሚታወስ ነው።
ይህን ተከትሎም በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ እየተሳተፈ የሚገኝ ሲሆን በመጀመሪያ ዙር ቅድመ ማጣሪያ የቻዱን ኤግሎንስን በድምር ውጤት 3 ለ 0 በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።
በያሬድ ገመቹ የሚመራው ሲዳማ ቡና በሁለተኛው ዙር ከአል ሂላል ኦምዱርማን ጋር ያደርጋል።
የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2018 የውድድር ዓመት በ47 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ሁለቱ ክለቦች ባለፈው የውድድር ዓመት በሊጉ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና ድል ቀንቶታል።
በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ስብስባቸውን ያጠናከሩት ሁለቱ ክለቦች የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌሎች መርሐ ግብሮች ሃዋሳ ከተማ ከመቻል በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እና ኢትዮጵያ ቡና ከሸገር ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተመሳሳይ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ሀዲያ ሆሳዕና ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በሆሳዕና አብዩ ኤርሳሞ ስታዲየም፣ አዲስ አዳጊው ጋሞ ጨንቻ ከኢትዮጵያ መድን በአርባምንጭ ዩንቨርሲቲ አባያ ካምፓስ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።