ከማዕድን ማውጣት እስከ ኢንዱስትሪ ሽግግር፤ የመደመር መንግሥት የማድረግ አቅም ማሳያ - ኢዜአ አማርኛ
ከማዕድን ማውጣት እስከ ኢንዱስትሪ ሽግግር፤ የመደመር መንግሥት የማድረግ አቅም ማሳያ
በመንግሥቱ ዘውዴ
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ
ኢትዮጵያ ካሏት ጸጋዎች መካከል የምድር ውስጥ ሃብቶች ይገኙበታል። ሃብቶቹ የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ ግብዓት ናቸው። እጅግ የበለጸጉ የጂኦሎጂካል ማዕድናት ሀብት ያላት ኢትዮጵያ የማዕድን ሃብት በብዝኅ ኢኮኖሚ መርህ የዕድገት ሽግግርን የሚያፋጥን መሰረት እየጣለ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ወርቅን ጨምሮ ለኢንዱስትሪና ለኮንስትራክሽን ዘርፍ በጥሬ ዕቃ ግብዓትነት የሚውሉ ውድና የከበሩ እንደ ታንታለም፣ ፖታሽና ሌሎች ማዕድናት በጉያዋ የታቀፈች ምድር ናት። ማዕድናት ለሥራ ዕድል ፈጠራም የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም።
በመደመር መንግሥት አምስት የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሮች መካከል የማዕድን ዘርፍ አንዱ እንዲሆን አድርጓል። ይህም የኢትዮጵያን የምድር ውስጥ እምቅ ሀብቶች ለኢኮኖሚ ዕድገት ማዋል እንደሚቻል ግልጸኝነትን የፈጠረ ወሳኝ እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል። በዚህም ባለፉት ዓመታት በዘርፉ ያሉ ሀብቶችን በማልማት፣ እሴት ጨምሮ በማምረትና ለገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገባት በኩል አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካን ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፤ ሀብቶቻችንን ከኢንዱስትሪ አቅም ጋር በማስተሳሰር የወጪ ንግድ ገቢንና የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ የጌጣጌጥ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍና ተወዳዳሪ የወርቅ እሴት ሰንሰለት ለመገንባት የመደመር መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።
የዚህ ሀገራዊ ጥረት አንድ አካል የሆነውና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ሥራ የጀመረው የቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካም የመደመር መንግሥት እምቅ የሀገር ሀብቶችን ለይቶ፣ አልምቶና አምርቶ ለውጤት ማብቃቱ አይነተኛ ምሳሌ ይሆናል። ይህ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስና በሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ መካከል በተደረገ አጋርነት የተቋቋሙ የመደመር መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ተዋንያን ጋር በጋራ በመሥራት የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳያል።
የማዕድን ሀብቶችን በማልማትና እሴት ጨምሮ በማምረት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ባለፉት ዓመታት በዘርፉ የተመዘገበውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ዕድገትም ሁነኛ አብነት ነው።
ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካም በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማንጠር አቅም አለው። ፋብሪካው በሀገር ውስጥ ምርት ላይ እሴት በመጨመርና የኢትዮጵያን የማዕድን ዘርፍ በማጠናከር በውድ ማዕድናት ማጣሪያ ረገድ ኢትዮጵያን ቀጣናዊ ማዕከል የሚያደርግ ትልቅ ምዕራፍ ሆኗል።
ከማዕድን ማውጣት እስከ ኢንዱስትሪ ሽግግር ድረስ በኢትዮጵያ የላቀ የእሴት ሰንሰለት እየፈጠረ ይገኛል። ይህ ፋብሪካም በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ርዕይ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ተደርጎ የሚወሰድ ተጨባጭ የልማት ውጤት መሆኑ እሙን ነው። የመደመር መንግሥት ኢንዱስትሪ ምርታማነትን ከማስፋፋት ባሻገር የማምረት አቅማቸው እንዲጎለብት የሰጠውን ትኩረት ያመላክታል።
የማዕድን ዘርፍ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቅድሚያ የሚሰጠው አምራች ዘርፍ እየሆነ መጥቷል። በተለይም የወርቅ ማዕድን ከፍተኛ ውጤት ማስገኘቱን ቀጥሏል። ይህ ሀገራዊ ተነሳሽነት ሀብቶችን ከሀገር ውስጥ ማቀነባበሪያ፣ ከኢንዱስትሪ አቅምና ከዘላቂ እሴት ፈጠራ ጋር ለማስተሳሰር የመደመር መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እንደሚያሳይም ያመላክታል።
የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካውም የወርቅ ጥራትን በማስጠበቅ ለማንጠርና ለውጭ ገበያ ዝግጁ ወደሆኑ ንጹሕ ምርት በመቀየር የጥራት ደረጃዎችን ለማሟላት ሁነኛ አቅም ይሆናል። የመደመር መንግሥትም ኢትዮጵያ ያሏትን ሀብቶች በጥሬው ለገበያ ከማቅረብ ይልቅ እሴት በመጨመር የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ የያዘውን ትክክለኛ የልማት አቅጣጫ ተጨባጭ ያደርገዋል።
ፋብሪካውም ኢትዮጵያ በሀብቶቿ ላይ እሴት ጨምራ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪነቷን ለማሳደግ በያዘችው የኢኮኖሚ አቅጣጫ መሰረት የተገነባው ነው። ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ ሥራ መጀመሩ የመደመር መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ግልጽና ትልቅ ርዕይ ማንገቡን ያመላክታል። በተለይም ለማዕድን ልማትና ዕድገት የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት የተመዘገበውን ውጤት በግልጽ የሚያሳይ ነው። ይህ ውጤታማ ተግባር በሌሎች ዘርፎችም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ትልቅ ሕዝብ ይዛ፣ ታላቅ ርዕይ የሰነቀችው ኢትዮጵያም የተፈጥሮ ሀብቶቿን በእውቀት፣ በቴክኖሎጂና በኢንዱስትሪ በማልማት ለሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ መሰረት እየጣለች ይገኛል። የብሔራዊ የከበሩ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ ሥራ መጀመርም ሃብትን በጥሬው ከመሸጥ ወደ እሴት ጨምሮ ማምረት ከዚያም ከሀብት ወደ ምርት፣ ከምርት ወደ ውጭ ንግድ ተወዳዳሪነት የሚያሸጋግር ጉልህ እርምጃ ነው። በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተፈጠረውን ዕድል በማስፋት ማዕድንን ጨምሮ የብዝኅ ኢኮኖሚ አዕማዶችን በማሳደግ የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢንና የሀገርን የምርት አቅም ማጠናከር የዚህ ርዕይ ዋነኛ መገለጫዎች ናቸው።
በርግጥም ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገርነትን ከትልቅ ሕዝብ፣ ጸጋዎችን ከልማት በማሰናሰል አቅምን ወደ ውጤትና ርዕይንም ወደ ተጨባጭ የብልፅግና መሰረት እየቀየረች ይገኛል።