በአፋር ክልል ለአረጋዊያን የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል ለአረጋዊያን የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ሠመራ፤ መሰከረም 30/2019(ኢዜአ)፡-በአፋር ክልል የአገር ባለውለታ የሆኑ አረጋዊያንን የመደገፍና የመንከባከብ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።
"እንክብካቤና ዘላቂ ደህንነት ለአረጋውያን ሰላማዊ ሕይወት" በሚል መሪ ሐሳብ በአፋር ክልል ደረጃ የዓለም የአረጋውያን ቀን ዛሬ በሰመራ ሎጊያ ከተማ ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ አሲያ ከማል እንዳሉት፣ አረጋውያን በጉብዝና ጊዜያቸው ለአገርና ለወገን ጠቃሚ ተግባራትን በማከናወን ሚናቸውን ተወጥተዋል።
ዛሬ በእርጅና ጊዜያቸው የሁሉንም ድጋፍና እገዛ እንደሚሹ ገልጸው፣ በክልሉ ህብረተሰቡንና የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ለአረጋውያን የሚደረገው ድጋፍና እንክብካቤ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ለዚህም ህብረተሰቡና ሌሎች አጋር አካላት የሚያደርጓቸውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል።
በዛሬው ዕለት በክልሉ በሚገኙ ከተሞች ከተውጣጡ የአረጋውያን ማህበራት ጋር በመሆን በዓሉ መከበሩን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ የማህበራዊ ዘርፍ ምክትል ኀላፊ ወይዘሮ ነስሮ ኡዳ ናቸው።
የአረጋዊያንን ቀን ምክንያት በማድረግ በአዋሽ ሰባት ከተማ ለሚገኘው "አቡነ አባቢ የአረጋውያን መርጃ ድርጅት" እና በአዋሽ አርባ ከተማ ለሚገኘው "አቡነ ዮናስ የአረጋውያንና ሕፃናት መርጃ ማዕከል" ለእያንዳንዳቸው 100 ሺህ ብር መለገሱን ገልጸዋል።
በቀጣይም ለአረጋዊያን በተለያየ መልክ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥል ብለዋል።
የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ ራሩባ መሐመድ በበኩላቸው በዛሬው ዕለት በከተማው ቤት ለቤት በመሄድ አቅመ ደካማ አረጋዊያንን መደገፋቸውን አንስተዋል።
በተመሳሳይ የዓለም የአረጋዊያን ቀን ከሰመራ ለጎጊያ ከተማ በተጨማሪ በክልሉ አሚበራ፣ አብአላ፣ ጎሊና፣ ደዌ እና ሲባቢ ወረዳዎችም ዛሬ ተከብሯል።
ቀኑ የተከበረው በዓለም ለ36ኛ ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ35ኛ ጊዜ መሆኑም ታውቋል።