ቀጥታ፡

ለመልካም ሕይወት- የአእምሮ ጤንነት

አእምሮ የሰው ልጅ የሚያስብበት፣ ስሜቱን የሚረዳበት፣ በራስ ህይወትም ይሁን በተለያዩ አጋጣሚዎች በሌሎች ላይ የሚወስንበት በመሆኑ የአይምሮ ጤና ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይነገራል።

የአእምሮ ጤና ሲጎዳ እነዚህና ተያያዥ ችግሮችን የሚያመጣ ብሎም የሥራ አፈጻጸም፣ የቤተሰብ ግንኙነት፣ የትምህርት ተሳትፎና የዕለት ተዕለት ኑሮ ሊነካ ይችላል። ስለዚህ ለአእምሮ ጤና የሚሰጠው ትኩረት እንደ አካላዊ ጤና ሁሉ ተመሳሳይ አስፈላጊነት ሊኖረው እንደሚገባ ይታመናል።

በመሆኑም እ.ኤ.አ. በየዓመቱ ጥቅምት 10 የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን ሆኖ ይከበራል። እለቱ የሚከበረው ለአእምሮ ጤና ተገቢውን ትኩረት ለመስጠት፣ ስለ ህመሙ በቂ ግንዛቤ እንዲኖር ለማድረግና ለታማሚዎች የድጋፍና እንክብካቤ ስራን ለማሳደግ መሆኑ ይነገራል።

የአእምሮ ጤና ችግር ሲነሳ በአንዳንዶች ዘንድ የተሳሳቱ አመለካከቶችና ግንዛቤዎች ይስተዋላሉ። የችግሩን መንስኤ ከድክመት፣ ከግል ባህሪ ወይም ከፈቃደኝነት ጉድለት ጋር በማያያዝ የተሳሳተ ትርጉም የሚሰጥበት ሁኔታ እውነታውን አያመላክትም።

የአእምሮ ጤና ችግር ከሥነ-ልቦናዊና ከማኅበራዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ሊከሰት የሚችልበት አጋጣሚም የሰፋ ነው። በውጥረትና የሕይወት ፈተናዎች ውስጥ ለረጅም ጊዜ መዝለቅ፣ የሚወዱትን ሰው በማጣት በሀዘን ውስጥ ለረጅም ጊዜ መዝለቅ፣ ግጭት፣ የኢኮኖሚ ችግርና ሌሎችም ምክንያቶች የህመሙ መንስኤዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ከመጠን በላይ ጭንቀትና ድብርት፣ ቀድሞ በደስታ ይሳተፍባቸው የነበሩ ነገሮች ላይ ፍላጎት ማጣት፣ የእንቅልፍ ለውጥ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ወይም መጨመር፣ የትኩረት ችግርና የተስፋ መቁረጥ ስሜት በተደጋጋሚ ከታዩ ለአይምሮ ህመም ሊያጋልጡ ይችላሉ።

የአእምሮ ጤና ችግር ውጤታማ የሆኑ የሥነ-ልቦና ሕክምናዎችና ሌሎች የሕክምና አማራጮች ያሉት ስለመሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት ይመክራል። የምክር አገልግሎት፣ የሥነ-ልቦና ሕክምና፣ በሀኪም ትእዛዝ መድኃኒት መውሰድና የማኅበራዊ ድጋፍ አገልገሎቶች መፍትሄዎች መሆናቸውንም ያመላክታል። 

በመሆኑም የአእምሮ ጤና ጉዳይ የጤና ተቋማት ብቻ ኃላፊነት ባለመሆኑ የቤተሰብ፣ የትምህርት ቤት፣ የሥራ ቦታ፣ የማህበራዊ ተቋማት፣ የሚዲያና ሌሎችም ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት ይመከራል።

በዚህ ችግር ውስጥ ያለን ሰው ስሜቱን ማክበር፣ ለባለሙያ እርዳታ እንዲያገኝ ማበረታታትና ከማኅበራዊ ግንኙነት እንዳይገለል ማድረግም አስፈላጊ ነው። የችግሩ ሰለባ የሆነን ሰው ማግለልና መሳለቅ ወይም ችግሩን በደካማነት መተርጎም ተገቢነት የለውም። በመሆኑም የዘንድሮው የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን የአእምሮ ጤና ችግር አጋጥሟቸው የነበሩ ሰዎችን ተሞክሮ ማጋራትና ለህመሙ ትኩረት በሚሰጥ መልኩ እየተከበረ ይገኛል።

በኢትዮጵያም የአእምሮ ጤናን ለማሻሻል የግንዛቤ ማሳደግ፣ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት፣ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን አቅም ማጠናከርና የማኅበረሰብ ድጋፍን ማሳደግ አስፈላጊ ይሆናል። በተለይም ከከተማ ርቀው በገጠር የሚኖሩ ህሙማን የአእምሮ ጤና ምርመራና የሕክምና አገልገሎት እንዲያገኙ መደገፍና ማበረታታት ይገባል።

አእምሮን የመንከባከብ ጉዳይ በሕክምና ብቻ ባለመሆኑ በቂ እንቅልፍ ማግኘት፣ አዘውትሮ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ጤናማ ምግብ መመገብ፣ ከቤተሰብና ከጓደኞች ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር፣ የዕረፍት ጊዜ መመደብና የውጥረት ምክንያቶችን በተቻለ መጠን መቀነስ እንደሚገባ ይመከራል። እነዚህ ልምዶች ግን በዘላቂነት የባለሙያ ሕክምናን የሚተኩ ባለመሆናቸው ተገቢውን ሕክምና ማድረግ የግድ ይላል።

የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን በዓመት አንድ ቀን የሚዘከር ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ በተግባር ሊተረጎም የሚገባ ማኅበራዊ ጉዳይ መሆን አለበት። ለአእምሮ ጤና ትኩረት መስጠት፣ ችግሮችን ቀድሞ ማወቅ፣ የሕክምና አገልግሎትን ማስፋት የተጎጂዎችን ክብር መጠበቅ እንደሚገባ ይመከራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም