ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በበጋ መስኖ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ይለማል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30/2019 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ የበጋ መስኖ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ዘንድሮ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በስፋት ይካሄዳል።

በክልሉ ዘንድሮ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት  ከ160 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

ከታቀደው መሬት እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ 400 ሺህ ሄክታር መዘጋጀቱን ጠቁመው ከዚህም ውስጥ 130 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የስንዴ ልማት ሥራዎች በሰፊው እና በተቀናጀ መልኩ ሲከናወኑ መቆየቱን ገልጸው ፣በዚህም አርሶ አደሩ ልምድና ክህሎት በማግኘት ከፍተኛ ተነሳሽነት እየጨመረ ነው ብለዋል።

የመስኖ የስንዴ ልማት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ለሀገር ውስጥ ፍጆታና ለውጪ ገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅምን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳለው አቶ በሪሶ አብራርተዋል። 

ልማቱ የአርሶ አደሩን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻል ባለፈ ለኢኮኖሚ ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የመስኖ ልማቱ የሚከናወነው በገጽ እና በከርሰ ምድር የውሃ አማራጮች በመሆኑ፣ ለአርሶ አደሩ በርካታ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች መቅረባቸውን አቶ በሪሶ አመልክተዋል ።

ከስንዴ ልማት ጎን ለጎን በመደበኛ የመስኖ ልማት መርሃ ግብር ከ500 ሺህ  ሄክታር በላይ መሬት ላይ  አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ገበያን ለማረጋጋት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

ለልማቱ ስኬታማነት ለአርሶ አደሩ አስፈላጊው የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና፣ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እየተደረገለት  መሆኑን ጠቁመው ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በበቂ ሁኔታ መቅረቡን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም