ቀጥታ፡

በክልሉ በህገወጥ የመድኃኒት እና የምግብ ምርቶች ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ ይቀጥላል

ጂንካ፤ መስከረም 30/2019 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጥራትና ደህንነታቸውን የጠበቁ የምግብና የመድኃኒት ምርቶችን ለህብረተሰቡ ለማቅረብ የክትትልና የቁጥጥር ሥራን አጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የጤና ቢሮው ምክትል ኃላፊና የምግብ፣ መድኃኒት፣ ጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች ቁጥጥር  ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ሶንቆ እንዳሉት፣ በክልሉ የቁጥጥር ስርዓትን በማጠናከር ጥራትና ደህንነታቸው የተጠበቀ የምግብና የመድኃኒት ምርቶች ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን እየተሰራ ነው።

ቢሮው የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው መዲኃኒቶችና የተሻጉ ምግቦች፣ ባዕድ ነገር የተቀላቀለባቸው ምግቦች እንዲሁም ህጋዊ ምዝገባ ባልተደረገባቸው መድኋኒቶች ላይ የተጠናከረ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ እንደሚያከናውን ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ በሚገኙ ከ2ሺህ 300 በላይ  የግል መድኃኒት ቤቶች ላይ በየጊዜው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደረግ ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመቱ ያለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ቢሮው ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻና ቁጥጥር ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ህገ ወጥ የመድሀኒት ምርቶች እና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የታሸጉ ምግቦች እንዲወገዱ ማድረጉን ገልፀዋል።

ህገወጥ ድርጊቱን በፈጸሙ የግል መድሃኒት ቤቶች እንደጥፋት መጠናቸው የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የመስጠት፣ የማሸግ እና በህግ ተጠያቂ የማድረግ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ዳይሬክተሩ አቶ ዮሴፍ አመልክተዋል።

በህገወጥ የመድሃኒት ቁጥጥር ሥራው የህብረተሰቡ ተሳትፎ የላቀ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣ በሦስት ወራት ውስጥ ብቻ 174 ጥቆማዎች ከሕብረተሰቡ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

 ፈዋሽነታቸውና ጤንነታቸው  ያልተረጋገጡ የመድኃኒትና የምግብ ምርቶች በህብረተሰቡ እና በሕጻናት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ መላው የክልሉ ህዝብ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም