በኢትዮጵያ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ጠንካራ የፍትህ ስርአት እየተገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ጠንካራ የፍትህ ስርአት እየተገነባ ነው
ባህር ዳር ፣መስከረም 30/2019(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ጠንካራ የፍትህ ስርአት እየተገነባ መሆኑን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች ገለጹ።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ጨምሮ የክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች በተገኙበት ሀገር አቀፍ የህግ ተርጓሚዎች ልዩ ጉባኤ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች በኢትዮጵያ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ጠንካራ የፍትህ ስርአት እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ኦቱከና ኦዳ (ዶ/ር)፤ የፍትህ አገልግሎት ወሰን የሌለው መሆኑን በመግለጽ በሁሉም አካባቢዎች ፍትሃዊ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።
የመድረኩም አላማ ይህንኑ ማስቀጠል መሆኑን አንስተው ለፍትህ መፋጠን፣ ጥራትና ተደራሽነት በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቆጭቶ ገብረማሪያም፤ የፍትህ ስርአቱ ማሻሻያ በነፃነት መስራት የሚያስችል አቅም መገንባቱ የሚጨበጥ ውጤት አምጥቷል ብለዋል።
ለዘርፉ ስኬት ተጠያቂነትና ግጽነት ባለው መልኩ ቀጣይነት ያለው የፍትህ ስርአት መገንባት ወሳኝ መሆኑን በማንሳት ለዚህም በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አለምአንተ አግደው፤ የፍትህ ስርአት ሪፎርም መከናወኑና በድጅታል አሰራር መታገዙ ወጪ ቆጣቢ፣ ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።
በክልሉም በዲጅታል ላይ የተመሰረተ ዳኝነት በተጠናከረ መልኩ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፤ የኢ-ፋይሊንግ አገልግሎቶችን በሁሉም ክልሎች ተደራሽ በማድረግ እንደ ሀገር ወጥ የሆነ አገልግሎት መስጠት እያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም የዜጎችን የፍትህ አገልግሎት ፈጣን፣ ቀልጣፋና ሚዛናዊ ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በቀጣይ ሀገር በቀል የተቀናጀ የፍርድ ቤቶች መረጃ አስተዳደር ስርአትን ወደ ስራ በማስገባት ዜጎች በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።