ቀጥታ፡

ኢሬቻ ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር በህዝቦች መካከል አብሮነት እንዲጎለብት እያደረገ ነው

አሶሳ፤ መስከረም 30/2019 (ኢዜአ)፦ ኢሬቻ ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር በህዝቦች መካከል አብሮነት እንዲጎለብት እያደረገ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ከማል ሀሰን ገለጹ።

በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የዘንድሮው እሬቻ በዓል "ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት" በሚል መሪ ሃሳብ በአሶሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።


 

በዓሉን አስመልክቶ በተዘጋጀ የፓናል ውይይት ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ከማል ሀሰን እንደገለጹት  ኢሬቻ የሰላም ፣ የአብሮነት እና የይቅርታ እሴቶችን የያዘ ነው ።

ኢሬቻ በህዝቦች መካከል ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ የይቅርታ እና የመከባበር እሴቶችን የያዘ በመሆኑ ለማህበረሰብ እሴት ግንባታ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።


 

በዓሉ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በድምቀት ሲከበር የህዝቦችን አብሮነት እና ባህላዊ እሴቶች እንዲተዋወቁ እያደረገ ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የጋምቤላ ክልሎች የጋራ የሰላምና ልማት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፍሮምሳ ሰለሞን በበኩላቸው፣ የኢሬቻ በዓል በአሶሳ ከተማ ለ6ኛ ጊዜ እየተከበረ መሆኑን ገልጸው፥ በዓሉ የጋራ የሆኑ የባህል እሴቶችን በማጎልበት እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ኢሬቻ የሰላም እና የወንድማማችነት በዓል በመሆኑ በዓሉን ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በአብሮነት እያከበሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተገኙ ሲሆን የኢሬቻ በዓል በነገው ዕለት በመልካ አሶሳ በድምቀት እንደሚከበር ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም