ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ለአዕምሮ ህመም የሕክምና አገልግሎት ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷል - ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤መስከረም 30/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ለአዕምሮ ህመም የሕክምና አገልግሎት ተገቢው ትኩረት መሰጠቱን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የአዕምሮ ጤና አገልግሎትን በማስፋት የአዕምሮ ጤና እክል ያጋጠማቸው ሰዎች መገለል እንዳይደርስባቸው ማኅበረሰባዊ ግንዛቤን ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ጥሪ ቀርቧል።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን ''እውነተኛ ድምፆች፤ ለእውነተኛ ለውጥ፤ የሕይወት ተሞክሮ ተደማጭነት ይረጋገጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል።


 

መሪ ሃሳቡም የአዕምሮ ጤና ችግር ያጋጠማቸውን ሰዎች የሕይወት ተሞክሮ ማዳመጥ፣ ድምጽ ማሰማትና የሕክምና አገልግሎትና ማኅበረሰብ ድጋፍ ክፍተቶችን ለመፍታት ያለውን ወሳኝ ሚና ያመለክታል።

በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሕይወት ሰለሞን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ ለአዕምሮ ጤና ሕክምና አገልግሎት ትኩረት ተሰጥቷል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የአዕምሮ ጤና ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት በተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑንም ገልጸዋል። 

ከአገልግሎት ተደራሽነት ማስፋት በተጨማሪ፣ በዘርፉ የሚታየውን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ ብቁ የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችሉ ተግባራትም እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በሀገሪቱ በሚገኙ የጤና ተቋማት የአዕምሮ ጤና ሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ሕብረተሰቡ ለአዕምሮ ጤና ችግር ሊያጋልጡ ከሚችሉ ሁኔታዎች በተለይም ከሱስና ሱስ አምጪ ነገሮች በመቆጠብ ጤንነቱን መጠበቅ እንደሚገባው አሳስበዋል።

የአዕምሮ ጤና ጥበቃ ማለት ሕክምና ከማግኘት በላይ ሰዎች ያለ ማኅበራዊ መገለልና ፍርሃት ስለ ሚያጋጥሟቸው ችግሮች መናገር የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠርንም ይጠይቃል። 

ስለሆነም የአዕምሮ ጤና ችግሮችን በተመለከተ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ማስወገድና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ያለ ማመንታት ወደ ሕክምና እንዲቀርቡ ማበረታታት ወሳኝ ነው።


 

የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር መገርሳ አለሙ በበኩላቸው፣ የአዕምሮ ጤና ችግሮች በተገቢው ሕክምና ሊድኑ የሚችሉ የጤና እክሎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአዕምሮ ጤናን የመጠበቅ ሥራ የአንድ ተቋም ወይም የጤና ባለሙያዎች ብቻ ኃላፊነት እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።

በዚህም ሕብረተሰቡ ግንዛቤውን በማሳደግ ለአዕምሮ ጤና እክል ላጋጠማቸው ሰዎች ተገቢውን ድጋፍ በመስጠት የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

የአዕምሮ ጤናን መጠበቅ የግለሰብ፣ የቤተሰብ፣ የጤና ተቋማትና የመላው ሕብረተሰብ የጋራ ኃላፊነት ነው ብለዋል።

የአዕምሮ ጤና ችግር ያጋጠማቸውን ሰዎች ድምፅ ማዳመጥ፣ ተደራሽና ጥራት ያለው ሕክምና ማስፋትና ማኅበራዊ መገለልን መቀነስ ጤናማና ተስፋ ያለው ማኅበረሰብ ለመገንባት ወሳኝ መሆናቸውን አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም