ቀጥታ፡

ማዕከሉ በምርምር ያወጣቸው የሩዝ ዝርያዎች የዝናብ እጥረትና በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት እያስገኙ ነው

ገንዳውኃ፣ መስከረም 30/2019(ኢዜአ)፡-የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር  ያወጣቸው የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎች የዝናብ እጥረት እና በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት እያስገኙ መሆኑን በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

​የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል በመተማ ንዑስ ማዕከል እያካሄደ ያለውን የሩዝ ዘር ብዜትና የሰብል ልማት ለአርሶ አደሮች፣ አመራሮችና የግብርና ባለሙያዎች ዛሬ አስጎብኝቷል።


 

በልማቱ እየተሳተፉ ያሉት ​የመተማ ወረዳ አርሶ አደር ጋሻው ሙሀመድ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ ያወጣቸው "ፎገራ-1" እና "አዝመራ" የተባሉ የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎች ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ ናቸው።

የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎቹ የዝናብ እጥረትን፣ በሽታን እና ሌሎች ችግሮችን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርትየሚያስገኙ በመሆኑ

የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር አህመድ ይመር በበኩላቸው፣ የሩዝ ልማቱ ከቤት ውስጥ የምግብ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ሃብት ለመፍጠር እያስቻላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል የመተማ ንዑስ ማዕከል አስተባባሪና ሰብል ተመራማሪ አቶ ግዛት አዱኛ፣ ማዕከሉ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማስተዋወቅ ሥራ ላይ ማተኮሩን ገልጸዋል፡፡

በተለይም በአንድ ሄክታር እስከ 55 ኩንታል ምርት የሚሰጡት የፎገራ-1 እና አዝመራ የተባሉ የሩዝ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት በምግብ ራሱን ከመቻል ያለፈ ለገበያ በማቅረብ ትርፍ ምርት እንዲያመርት ለማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። 

​የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ጤናው ፈንታሁን በበኩላቸው እንዳሉት፣ በዞኑ የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎችን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ ያለው ሥራ  ውጤት አምጧል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም